ቀጥታ፡

ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲስፋፋ ቁልፍ ሚና መጫወት ይችላሉ ተባለ

ሰኔ 7/2011 የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች የክረምትና በጋ በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ተሳትፎ ማህበረሰቡ አገልግሎቱን በስፋት እንዲሰጥ መነሳሳትን የሚፈጥር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የላቀ ተግባር ላከናወኑ ወጣቶች የምስጋና እና እውቅና መርሃ ግብር ዛሬ አካሂዷል። በዚሁ ወቅትም ባለፈው ዓመት ለተሳተፉ በጎ ፍቃደኞች ሽልማት ተበርክቷል፤ ላከናወኑት በጎ ተግባርም አስተዳደሩ በነዋሪው ህዝብና በመንግስት ስም ምስጋና አቅርቧል። የማስተባበሪያው ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ትዕዛዙ በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተገለፁት በአዲስ አበባ ብቻ ላለፉት 16 አመታት በርካታ የልማት ተግባራት የተከናወኑበት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ተሰጥቷል፤  በዚህም 850 ሺህ የሚልቅ ዜጋ ተሳትፏል። በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶቹም ደጋፊ ለሌላቸው አረጋዊያንንና ተማሪዎች የሰብአዊ እርዳታ ማቅረብን ጨምሮ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ፣ ችግኝ ተከላ፤  የደም ልገሳ ተግባራት መከናወናቸውን አቶ አክሊሉ ተናግረዋል። በተለይም ባለፈው ዓመት የክረምትና በጋ ወቅት ብቻ በከተማው የሚኖሩ 600 የሚጠጉ ረዳት የሌላቸው አረጋዊያን መኖሪያ ቤቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መታደሳቸውን አክለዋል። በእነዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብሮች ከወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳትፈዋል። አቶ አክሊሉ እንዳሉት በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስልጣን ላይ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እያከናወኗቸው ያሉት የተለያዩ የማህበራዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ተነሳሽነት እየፈጠረ ይገኛል። በመሆኑም የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች በዚህ ተግባር መሳተፍ ተግባሩ እንዲጠናከር የሚያስችል መነሳሳትን በማህበረሰቡ ዘንድ የሚፈጥር በመሆኑ በበለጠ መጠን ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል። በምስጋና መርሃ ግብሩ ተሸላሚ የሆኑት በጎ ፈቃደኛ አቶ ተረፈ ሰይፉ እንደሚሉት  አገልግሎቱን በሚሰጡበት ወቅት የአቅርቦት ችግር ይገጥማቸው ነበር፤ ይህ የአቅርቦት  ችግር ይቃለል ዘንድ መላው ዜጋ በተለይም ወጣቶች ባላቸው እውቀት፣ ጉልበትና ሙያ መሳተፍ አለባቸው። የዘንድሮውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሃምሌ 2011 ዓም እስከ መስከረም 17/2012 ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በዘንድሮው መርሃ ግብር ከከዚህ ቀደሞቹ ተግባራት ባሻገር አረጋዊያንን መንከባከብና 500 ያረጁ ቤቶችን ማደስን፣ የቋንቋና የኮምፒዩተር ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቋል። ለጤና አስከፊ የሆኑ የከተማው አካባቢዎችን የማፅዳትና የማስዋብ ሥራም ይከናወናል ተብሏል። በአዲስ አበባ ለ17ኛ ጊዜ በሚካሄደው የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በጠቅላላው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመላው ኢትዮጵያ ዘንድሮ በሚካሄደው አገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዬን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታውቋል። መርሃ ግብሩ በ13 የስምሪት ዘርፎች የሚሰማሩት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባር ያከናውናሉ፤ ይህም  በገንዘብ ሲተመን የ6.4 ቢሊዮን ብር ይገመታል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም