የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው
ሰኔ 7/2011 የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣዩ ሳምንት ይካሄዳል። ሳምንቱ "የውሃና ኢነርጂ ዘርፎች ትራንስፎርሜሽን ለአዲሲቷ የተስፋ አድማስ" በሚል መሪ ሐሳብ ከሰኔ 10 እስከ 13 ቀን 2011 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች የሚካሄድ ይሆናል። የውሃ መስኖና ኢኒርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንትን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ መግለጫ ሰጥቷል። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሳምንቱን የመካሄድ ዓላማ ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብቶች ወደ ተለያዩ ልማቶች በመቀየር ተጠቃሚ በምትሆንበት ሁኔታ ላይ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ መስኮች እየተገበረች ባለችው ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎችና ሌሎች መርሃ ግብሮች ላይም የባለድርሻ አካላትን ሙያዊ ሀሳቦችን ለመሰብሰብ ሳምንቱ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች ባሉ ተግዳሮቶችና መልካም እድሎች፣ በመንግስትና በግል አጋርነት አማካኝነት በሚካሄዱ የዘርፉ የግንባታ ስራዎችና ህብረተሰቡ በውሃና ኢነርጂው ዘርፍ ያላት ተጠቃሚነት ዙሪያም ምክክር ይደረጋል ብለዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመታት በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ዘርፎች ለማከናወን ያቀደችውን ስራዎች በተመለከተም የተዘጋጀው ረቂቅ ስትራቴጂ በምክክር መድረኩ ቀርቦ ከዘርፉ ባለሙያዎች ግብዓት እንደሚሰበስብም አመልክተዋል። ረቂቅ ስትራቴጂው የተዘጋው ከዚህ በፊት በዘርፉ ከተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮችን በመገምገም መሆኑንም ገልጸዋል። በሁለተኛው የ'ዋን ወሽ' መርሃ ግብር፣የወጣቶች መስኖ ልማት መርሃ ግብር፣ ብርሃን ለሁሉ ሁለተኛው የኤሌትሪፊኬሽን መርሃ ግብር፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይም ምክክር እንደሚካሄድም ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት። ኮይሻና ሌሎች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እያደረጉባቸው ስላሉ የታዳሽ ሃይል ልማት ፕሮጀክቶች፣ የ4 ቢሊዮን የዛፍ ቸግኞችን በመትከል ከተሞችንና ገጠር አካባቢዎችን ወደ አረንጓዴ የማሸጋገር እቅድና ሌሎች መርሃ ግብሮች ላይ ውይይት ይደረጋል ብለዋል። በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ከዘላቂ የልማት ግቦች እና ከአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብሮች ጋር ያለውን ቅንጅት ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ምክክር እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት በዘርፉ ጉዳዮች ላይ የጎንዮሽ ውይይቶች፣ አውደ ርዕዮችና ትዕይንቶች አንደሚካሄዱና ለስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች የሚሆኑ ምክረ ሀሰቦች እንደሚገኙበትም ይጠበቃል። በውይይት መድረኮቹ ላይ የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት፣ ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት፣ ከዩንቨርስቲዎችና ምርምር ማዕከላት የተወጣጡ ምሁራን፣ የግሉ ዘርፍ፣ አጋር ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እና ሌሎች ተቋማት እንደሚሳተፉም ገልጸዋል። በተያያዘ ዜና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የሃይል ማመንጫ ግድቦች እያቀረቡ ያለው የሃይል ምርት በአሁኑ ሰዓት ያለውን የፈረቃ የኤሌትሪክ አገልግሎት ማስቀረት የሚያስችል እንዳልሆነ ተናግረዋል። በሃይል ማመንጫ ግድቦቹ የውሃ ማጠራቀሚዎች ውስጥ ውሃ በጥሩ ሁኔታ እየገባ ቢሆንም በውሃ ማጠራቀሚዎቹ ከፍታ በሚፈለገው ደረጃ ባለመጨመሩ የሚፈለገውን ያህል ሃይል ማምረት እንዳልታቸለ ገልጸዋል። ሃይል በበቂ ሁኔታ ማመንጨት የሚቻለው የውሃ መጠንና ከፍታ ጥመርታ ሲመጣጠን መሆኑንና አሁን ባለው ሁኔታ የውሃ ከፍታው መጠን ዝቅተኛ እንደሆነ አስረድተዋል። አሁን ያለው እየጣለ ያለው ዝናብ በግድቦቹ ውሃ እንዲሞላ በጥሩ ሁኔታ እየረዳ እንደሆነና ያም ቢሆን አሁንም በግድቦቹ ያለው የውሃ ማጠራቀሚያዎች ፈረቃውን ማስቀረት የሚያስችል አቅም ላይ አልደረሱም ብለዋል። ከግንቦት 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ በአገር አቀፍ ደረጃ የኤሌትሪክ ሃይል የፈረቃ አገልግሎት ተግባራዊ እየሆነ እንደሆነ ይታወቃል።