የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ
ሰኔ 7/2011 የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ። በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ እና ወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ የሊጉን አሸናፊ ይለያል፡፡ ሮቤ ላይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ማን እንደሚሆን የሚለይበት ወሳኝ ጨዋታ ነው። ወላይታ ድቻ ፕሪሚየር ሊጉን በ34 ነጥብ እየመራ ሲሆን መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ32 ነጥብ ይከተላል። እስከ መጨረሻው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ባልተለየበት የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከወዲሁ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። በፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ደንብ መሰረት በቮሊቦል ጨዋታ 3 ለ 0 ወይም 3 ለ 1 የሚያሸንፍ ክለብ ሶስት ነጥብ የሚያገኝ ሲሆን 3 ለ 2 ካሸነፈ ደግሞ አሸናፊው ክለብ ሁለት ነጥብ ተሸናፊው ክለብ አንድ ነጥብ ያገኛል። በዚሁ መሰረት በእሁዱ ጨዋታ ወላይታ ድቻ 3 ለ 0 ወይም 3 ለ 1 ማሸነፍ እንዲሁም 3 ለ 2 መሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ያደርገዋል። ተጋጣሚው መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ለመሆን ወላይታ ድቻን 3 ለ 0 ወይም 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ወረቀት ላይ ባለው ሂሳባዊው ስሌት መሰረት ወላይታ ድቻ ከመዳወላቡ ዩኒሸርሲቲ የተሻለ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ የመሆን እድል ያለው ቢሆንም ሁለቱ ክለቦች ካላቸው ወቅታዊ አቋም አንጻር በጨዋታው ብርቱና ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት መገመት ይቻላል። ወላይታ ድቻ መዳወላቡ ዩንቨርስቲን ካሸነፈ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን አሸናፊ መሆን የሚችል ሲሆን መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ በሂሳባዊው ስሌት የሚጠበቅበትን ውጤት ካስመዘገበ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ይሆናል። ከሳምንቱ የፕሪሚየር ሊጉ ተጠባቂ ጨዋታ በተጨማሪ ከነገ በስቲያ በ14ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሶስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ሙገር ሲሚንቶ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከረፋዱ አራት ሰዓት ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከመከላከያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ባህርዳር ላይ ጣና ባህርዳር ከአዲስ አበባ ፖሊስ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ደቂቃ ላይ የሚደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በስፖርቱ አፍቃሪ ዘንድ የሚጠበቅ ነው። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፕሪሚየር ሊጉን በ30 ነጥብ ሲመራ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ26 ነጥብ ይከተላል። የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተጋጣሚውን ቂርቆስ ክፍለ ከተማን ካሸነፈ የሊጉ አሸናፊ የሚሆንበትን እድል በሰፊው የሚያሰፋ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የጨዋታ አሸናፊ ከሆነ የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ በማድረግ የዋንጫ ፉክክሩን ተጠባቂ ያደርገዋል። ሁለቱ ክለቦች ካላቸው ወቅታዊ አቋም አንጻር ጨዋታው ተመጣጣኝ እና ብርቱ ፉክክር ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል። ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከመከላከያ ከነገ በስቲያ መቐለ ላይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከከምባታ ዱራሜ ይጫወታሉ። ፌደራል ፖሊስ ከቡታጅራ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ቡታጅራ ከተማ በጨዋታ ሜዳዎች ላይ ባለመገኘት በተደጋጋሚ ጊዜ የፎርፌ ውጤት እየተሰጠበት በመሆኑ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጪ እንዲሆንና በቀጣይ ከክለቡ ጋር ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች በፎርፌ ውጤት እንዲያገኙ ባለፈው ሳምንት መወሰኑ ይታወሳል። በዚሁ መሰረት ፌደራል ፖሊስ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝቷል። ድሬዳዋ ከተማም በፋይናንስ ችግር ምክንያት ራሱን ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በውድድሩ ደንብ መሰረት ከድሬዳዋ ጋር ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች የፎርፌ ውጤት እያገኙ ነው። ጎንደር ከተማ በ18ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ የማያደርግ በመሆኑ አራፊ ክለብ ነው። ድሬዳዋ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ በሊጉ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ብሏል።