ቀጥታ፡

የብራና መዛግብት ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው አይደለም ተባለ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ የብራና መዛግብት ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው አለመሆኑ ተገለጸ። ጥንት አባቶች በብራና፤ ቀለም በጥብጠው ለአያሌ ዓመታት የደከሙባቸው የብራና መጻሕፍትና መዛግብት በተለያዩ ዘመናት በውጭና በውስጥ ጠላቶች ለዘረፋና ስርቆት ተጋልጠው በየአገራቱ አብያተ መጻሕፍትና ቤተ-መዘክራት እንደሚገኙ ይታወቃል። ከዘረፋና ከጥፋት የተረፉ በርካታ ጥንታዊ የብራና መዛግብትና መጻሕፍት ግን በአገር ውስጥ በሚገኙ መንግስታዊና ኃይማኖታዊ ተቋማት ውስጥ እንዳሉ እሙን ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ ጥበቡ አንተነህ፤ 'የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ጥበቃ አንድምታ' በሚል ባደረጉት ጥናት የብራና መዛግብትና መጻሕፍት ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ መመልከታቸውን በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል። የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ፤ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋምና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ-ፓትሪያርክ ቤተ-መጻሕፍት በጥናቱ ተዳስሰዋል። ከመንበረ-ፓትሪያርክ ቤተ-መጻሕፍት በስተቀር የተቀሩት በተልዕኮና በዓላማ የተቋቋሙ መንግስታዊ ተቋማት መሆናቸውን ይገልጻሉ። ተቋማቱ ውድና በብዙ ድካም የተገኙ የብራና መጻሕፍትን መጠበቅና ለጥናትና ምርምር ክፍት ማድረግ አንዱ ተልዕኳቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በጥናታቸው እንዳረጋገጡት "የብራናዎቹ አቀማመጥ፣ አያያዝና የጥበቃቸው አንድምታ አሉታዊና ለጉዳት የሚዳርግ ነው" ብለዋል። "ብራናዎች በትክክል በቁጥር አይታወቁም፤ በዲጂታል መንገድ አልተቀመጡም" ያሉት አቶ ጥበቡ፤ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ብቻ 400 የብራና መጻሕፍት ያረጁ፣ ቀለማቸው የጠፋና እድሳት የሚያሻቸው እንደሆኑ መታዘባቸውን ተናግረዋል። በሁሉም ተቋማት የጥገናና እድሳት አገልግሎት አለመኖሩንም አንስተዋል። መጻሕፍቱን በፎቶ ወይም በዲጂታል የንባብ መንገድ ማዘጋጀት ብዙ ሰው ለማስተናገድና ከእጅ ንክኪ ነጻ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ነገር ግን ከአንድ ተቋም በስተቀር ሁሉም በፊልም የንባብ አገልግሎት እንደሌላቸውም ገልጸዋል። በተመረጡ ተቋማት ያለው የብራና አያያዝ ለአጥኚዎች የማይመችና ለጥናትና ምርምር የማያበረታታ መሆኑንም ገልጸዋል። "መጠበቅ ማለት መዛግብቱን ቆልፎ ማስመቀጥ አይደለም" የሚሉት አቶ ጥበቡ፤ ከቆዳ የተዘጋጁ ብራናዎች በጸሐይና ሙቀት በቀላሉ እንደሚጎዱ አብራርተዋል። ስለሆነም ለብራና መጻሕፍት በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ ዲጂታላይዝድ ጥበቃ በመስጠት ለገቢ ማስገኛ ማዋልና ለአንባቢና ተመራማሪዎች ክፍት በማድረግ ለዕውቀት ምንጭነት መጠቀም እንደሚገባ ነው ያወሱት። በብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሃፍት ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታዬ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፣ ጥንት ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ማንኛውንም ጥልቅ የዕውቀትና ጥበብ ምስጢራት በብራና መጻሕፍት ላይ ማስፈራቸውን ያነሳሉ። እነዚህን ዕውቀቶች ወደሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የብራና መዛግብትና መጻሕፍትን በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ኤጀንሲው ብራናዎችን የማሰባሰብ፣ የማደራጀት፣ የመጠበቅ፣ ለጥናትና ምርምር የማዋልና ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንደተሰጠው ያምናሉ። በኤጀንሲው የሚገኙ በርካታ የብራና መጻሕፍት በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች እንዳይጎዱ የመጠበቅ፣ ደረጃውን በጠበቀ ቦታ የማስቀመጥ፣ በዲጂታል መንገድ ለጥናትና ምርምርና ለንባብ ክፍት የማድረግ ስራዎች እንዳሉም ነው የሚገልጹት። ኤጀንሲው በአገር ውስጥ ካሉ ሌሎች ተቋማት በንጽጽር የተሻለ ቢሆንም የብራና ሀብቶቹ "ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አያያዝና ጥበቃ አላቸው ማለት አንችልም" ብለዋል። ኤጀንሲው ደረጃውን ያሟላ ጥበቃ ለመዘርጋት የክምችት ብዛትና የቢሮ ጥበት ችግር እንዳለበት ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመፍታት በሚቀጥለው ዓመት የሚጠናቀቅ ባለ 13 ፎቅ ሕንጻ እያስገነባ መሆኑንም ተናግረዋል። በሌላ በኩል አብዛኞቹ የብራና መጽሐፍት ባለቤትና ተጠቃሚዎች ኃይማኖታዊ ተቋማት በመሆናቸው ወደ ኤጀንሲው ክምችት ለማምጣት ችግር እንዳለ ጠቅሰው፤ መጽሃፍቱ ደረጃውን ባሟላ ቦታ እንዲጠበቁና ከጥፋትና ስርቆት ለመታደግ የቆጠራና ማስመዝገብ ስራዎች እንዲሰሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያብራሩት። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው የጽሁፍ ሀብቶች መካከል አብዛኞቹ በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ የብራና ድርሳናት ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም