ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት ኮንፍረንስ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው

ሐረር  ሰኔ 1/2010 የኅብረት ስራ ማህበራትን የስራ እንቅሰቃሴ ለማጎልበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የታገዘ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ የግብርና  እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ገለጸ። 3ኛው የኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት ኮንፍረንስ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው። የግብርና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በኮንፈረንሱ ላይ እንደገለጹት የህብረት ስራ ማህበራት የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦትና አገልግሎት በማስፋፋት፣ የግብርና ልማት ስራን በማዘመን፣ ምርታማነት እንዲያድግ የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እያደረጉ ነው፡፡ እንዲሁም አምራቹና ሸማቹ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን፣ የገጠርና ከተማ ትስስር እንዲጠናከር፣ ጤናማ የገበያ ስርዓት በመገንባትና ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ገልፀዋል፡፡ የኅብረት ስራ ማህበራት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊና እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዎ እያበረከቱ ቢሆንም የሚጠበቅባቸውን ውጤት ከማስገኘት አንጻር ግን ብዙ ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በማህበራቱ ላይ የሚታዩ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ውስንነቶችንና የቅንጅታዊ አሰራር ችግር በጥናት በመለየት መፍትሄ በማስቀመጥ ረገድ ሊያግዟቸው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ የኢፌዴሪ የኅብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙሐመድ በበኩላቸው በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ከ84ሺ 385 የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖች ይገኛሉ። ከ19 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ አባላት ያላቸው የህብረት ሰራ ማህበራት በግብርና ግብይትና የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር፣ በገንዘብ ብድርና ቁጠባ፣  በሸማቾች ህብረት ስራና በሌሎች የስራ ዘርፎች ተደራጅተው ህብረተሰቡን በተለይ ደግሞ አርሶ አደሩን እያገለገሉ  ይገኛሉ። በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ተጨባጭ ውጤት ለማጠናከርና ሁሉም አካላት በቀጥታ የተሳተፉበት የኅብረት ስራ ልማት ረቂቅ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ስራ ለመግባት እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። 'የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከሚሰራቸው የማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ የህብረት ስራ ማህበራትን ማደራጀትና ማስልጠን ይገኝበታል'' ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ናቸው፡፡ በተለይ ዩኒቨርሲቲው በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን የምርጥ ዘር አቅራቢ የአርሶ አደር ማህበራትን በማደራጀት ምርጥ ዘር ለሌሎች አርሶ አደሮች እያሰራጩ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ በስልጠና ረገድም ዩኒቨርሲቲው  በተሻለ ሁኔታ ሰርቶ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በተደጋጋሚ ጊዜ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም በተለይ የማህበራቱን አቅም ለማጎልበት  ከኅብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ጋር እያከናወነ የሚገኘውን የጥናትና ምርምር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል የኅብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሽፈራው  "በክልሉ በማህበራቱ ላይ የሚያጋጥሙ የሙያ፣ የፋይናንስ፣ የሎጀስቲክስና የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር በመቅረፍ ረገድ የሚታዩ ውስንነቶችን ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች በሌሎች አካባቢዎችም  ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው" ብለዋል። ''የኅብረት ስራ ማህበራት ምርትና አገልግሎት ውጤታማነት ለዘላቂ ተጠቃሚነት'' በሚል መሪ ቃል ለሦስት ቀናት በተዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ  የሁሉም ክልልና ከተማ መስተዳድር የሚገኙ የህብረት ስራ ኤጀንሲና መልካም ተሞክሮ ያላቸው የህብረት ስራ ማህበራት ተገኝተዋል፡፡ በኮንፈረንሱ መክፈቻ እለትም ስድስት ጥናታዊ ጽሁፎችና ተሞክሮዎች በባለሞያ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም