ቀጥታ፡

የፈጠራ ስራዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ ድጋፍ ማዕቀፎችን አዘጋጅተናል-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

ሰኔ 5/2010 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለፈጠራ ስራዎች እውቅና ከመስጠት ባለፈ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያግዙ ፋይናንስን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ዛሬ ባካሄደው ዘጠነኛ ዙር አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽልማት ለአንድ መቶ ዘጠና አራት የፈጠራ ባለቤቶች ሽልማት የሰጠ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 24ቱ ሴቶች ናቸው። ይህም ሚኒስቴሩ ለዘጠኝ ዙር ባካሄደው አገር አቀፍ የፈጠራ ስራ ሽልማትና እውቅና ያገኙ ዜጎችን ቁጥር 1 ሺህ 887 አድርሶታል። ነገር ግን  አብዛኛዎቹ ተሸላሚዎች ከእውቅና ስነ-ስርዓት በኋላ የፈጠራስራዎችን  ለማህበረሰቡ ተደራሽ ሲያደርጉ አይታዩም። ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሸላሚዎች እንደሚሉት፤ ለፈጠራ ባለቤቶች ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል ስለማይደረግላቸው የፈጠራ ስራና ማህበረሰብ በሚፈለገው ደረጃ ሊተሳሰሩ አልቻሉም። ካለኤሌክትሪክ ኃይል የአልባሳት ላይ ህትመትን ማከናወን የሚችል ማሽን የፈጠረው ወጣት ታረቀኝ ሽፈራው የፈጠራ ባለሙያዎች የፋይናንስ ችግሮቻቻውን መቅረፍ የሚያስችል ስልጠናን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ስለማያገኙ ስራዎቻቸውን ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዳያደርጉ ማነቆ መፍጠሩን ይገልጻል። እርሷን ጨምሮ ከአምስት እንስት ጓደኞቿ ጋር በመሆን የእናቶች ምጥን መከታተል የሚያስችል ማሽን መፍጠር የቻለችው ወጣት ሊዲያ ውብሸት በበኩሏ የፈጠራ ስራዎቸን በቀላሉ ወደ አገልግሎት ማስገባት የሚያስችል የተቀናጀ አሰረር አለመኖሩን ተናግራለች። የእነርሱን የፈጠራ ውጤት የትወስደው ሙከራ ማድረግ እንደሚችሉ እስካሁን አለማወቃቸውን ለአብነት በመጠቆም። በሚኒስቴሩ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ በተለይ ለኢዜአ አንደተናገሩት፤ የፈጠራ ስራ ተሸላሚዎች አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ሲደረግላቸው አልነበረም። ሚኒስቴሩ የነበሩትን አሰራሮች በመቀየር የፈጠራ ስራዎች ወደገበያ እንዲያቀርቡ አስፈላጊውን ደጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ ድጋፉም ፋይናስን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን ያካትታል ብለዋል። ድጋፉ በተለያያ አካባቢዎች በተገነቡ የፈጠራ ስራ ማበልጸጊያ ማዕከላት አማካኝነት እንደሚደረግ ነው ያወሱት። የፈጠራ ባለቤቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የህግ ማዕቀፍም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል። የኤሌክትሮኒክስ ግበይት ስርዓትን የሚመለከተ ህግ መዘጋጀቱንም ለአብነት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም