በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ የነበሩ መልካም እሴቶች እየተሸረሸሩ መጥተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ የነበሩ መልካም እሴቶች እየተሸረሸሩ መጥተዋል
ሰኔ 5/2011 በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዓመታት በገበያ ስርዓት ውስጥ የነበሩ መልካም እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነጋዴዎችና ሸማቾች ገለጹ። አለመተማመንና እየባሰበት የመጣው የኑሮ ውድነት ደግሞ ለእሴቱ መሸርሸር ዋነኛ መንስኤ መሆናቸውንም አንስተዋል። የኢትዮጵያ የግብይት ታሪክ ዕቃን በዕቃ በመለዋወጥ መጀመሩን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። አሞሌ ጨው፣ የማሪያ ትሬዛ ታበር ወይም ብር የወርቅ የብርና የመዳብ ሳንቲሞች ደግሞ የወረቀት ገንዘብ ስራ ላይ እስኪውል ድረስ ግብይት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል። በዘመኑ ዕቃዎቹ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው መሆን አለመሆናቸው እንኳን በአግባቡ ባይረጋገጥም ዕቃን በዕቃ በመለዋወጥ ግብይት ይፈጸም ነበር። በገንዘብ መገበያየት ከተጀመረ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮም አንድ ነጋዴ ኪሳራ ሲደርስበት ሌሎች ነጋዴዎች ገንዘብ በማሰባሰብ ተመልሶ እንዲያንሰራራ ይደጋገፉ፣ ይተባበሩና ይተዛዘኑ እንደነበርም ይነገራል። በሌላ በኩል ሸማቹ እጅ ሲያጥረው ነጋዴው በእምነት የሚፈልገውን ዕቃ ያበድረዋል፣ ተበዳሪውም ባለበት ጊዜ ይመልሳል፤ የዱቤ ግብይትም ይሰኝ ነበር። ለመሆኑ እነዚህን የመሳሰሉት የገበያ ውስጥ እሴቶች በአሁን ጊዜ አሉ ወይ? ብሎ ኢዜአ ነጋዴዎችንና ሸማቾችን አነጋግሯል። ከልጅነቱ ጀምሮ በንግድ ስራ ላይ መሰማራቱን የሚገልጸው አቶ አማረ ጥላሁን በነጋዴው መካከል የመደጋገፍና የመተጋገዝ ባህሉ ቀደም ሲል በነበረው ልክ ተጠናክሮ ባይቀጥልም ጨርሶ ግን አልጠፋም ይላል። እርስ በእርስ መተማመኑ እየተሸረሸረ የሄደውም ከኑሮ ጫና ጋር ተያይዞ እንደሆነ በማውሳት። ቀደም ሲል በዱቤ ዕቃ በመስጠት ኪሳራ የገጠመው ነጋዴ እንዲነሳ የማድረግ እሴቱ አሁን እየቀረ መምጣቱን የሚናገሩት ደግሞ አቶ ሽመልስ አበራ ናቸው። ሸማቾችም ቢሆኑ ቀደም ሲል በሻጭና ገዥ መካከል የነበረው የመተማመንና የመተዛዘን መልካም እሴት በአሁኑ ጊዜ መሸርሸሩን አንስተዋል። ሸማች አቶ ወርቁ ገብረመድህን በበኩላቸው የሌለው ሰው ካለ ተበድሮ ልብስ ይለብሳል ለልጆች ደብተር ይገዛል ይሄ ዋስ አያስፈልግም ፊርማ አያስፈልግም በእምነት ዛሬ 15 አመጣለሁ ያለ በ15ቱ ያመጣል። የዛሬ ወር አመጣለሁ ያለ በወሩ ያመጣል። አሁን በፊርማም ተደርጎ በነባሪም ተደርጎ ይሄ የለም ብለዋል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሽዮሎጂ መምህር ዶክተር አበጀ ብርሃኑ ቀደም ሲል በአገሪቷ ንግድ በትንሽ ገንዘብ የሚጀመር መሆኑን ያስታውሳሉ። በአሁኑ ጊዜ ግን የንግድ ልውውጡም ሆነ ንግድ ለመጀመር የሚያስፈልገው ካፒታል ከፍተኛ በመሆኑ አንዱ ነጋዴ ከሌላው ጋር የነበረው የጠበቀ ግንኙነት እየላላ መምጣቱንም ነው የገለጹት። በገበያ አካባቢ የሚታየው ራስ ወዳድነትና አለመተማመን የመጣውም ከንግድ ዕድገት ጋር ተያይዞ መሆኑንም አንስተዋል። የሰው ልጅ በህይወት እስካለ ድረስ መተሳሰብ መተማመንና መረዳዳት ሊኖር የሚገባው መልካም እሴት በመሆኑም ሁሉም ሰው እነዚህ እሴቶች እንዳይጠፉ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት።