ቀጥታ፡

ፓልም ዘይት በረጅም ጊዜ አጠቃቀም የሰውነትን የኮሊስተሮል መጠን እንደሚጨምር ተገለጸ

ሰኔ 5/2011 ፓልም የምግብ ዘይት በረጅም ጊዜ አጠቃቀም በሰውነት ውስጥ የኮሊስትሮል መጠን በመጨመር በጤና ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ። ፓልም ዘይት በጤና ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የጤና ችግር ለመከላከልም መንግስት የአገር ውስጥ ዘይት አምራቾችን ማበረታታት እንዳለበትም አሳስቧል ኢንስቲትዩቱ። ኢትዮጵያ በዓመት ከስምንት እስከ ዘጠኝ ቢሊዬን ብር ወጭ እያደረገች ከውጭ የምታስገባው በተለምዶ የሚረጋው ዘይት የሚባለው ፓልም ዘይት ነው። በኢትዮጵያ ለምግብነት ከሚውሉ 16 የምግብ ዘይት አይነቶች 81 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው ፓልም ዘይት አንደሆነም የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያሳያል። በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ ያሉ የምግብ ዘይቶችን አለም ዓቀፍ ደረጃ፣ የምግብ ይዘታቸውና በጤና ያላቸው ተጽዕኖ በተለመከተ መግለጫ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንዳሉት፤ ኅብረሰተቡ ፓልም ዘይትን ያለማቋረጥ የመጠቀም ልምዱ ከፍተኛ ነው። ፓልም ዘይት የሰው ልጅ ከሚያስፈልገው የፋቲ አሲድ ክምችት (saturated faty acid) ሁለትና ሶስት እጥፍ የያዘ መሆኑንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው በዋጋ ቅናሹንና የጥራት ደረጃው ዝቅ ያለው ፓልም ዘይት በመሆኑም የፋቲ አሲድ ክምችት ይዘቱ 50 በመቶ ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ የፓልም ዘይትን በተከታታይ ያለ ማቋረጥ የሚጠቀሙ ዜጎችን የኮሊስትሮል መጠን በመጨመር ለበሽታ ያጋልጣል ነው ያሉት። መንግስትም የፓልም ዘይትን የረጅም ጊዜ አጠቃቀም ዜጎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት አማራጭ መንገዶችን መጠቀም እንዳለበት አሳሰበዋል። አገሪቷ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ 2017 ብቻ 450 ሜትሪክ ቶን ዘይት ኅብረተሰቡን ለመደጎም ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ አስገብታለች። በመሆኑም በረጅም ጊዜ አጠቃቀም በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የጤና እክል ለመከላከል ከውጭ የሚገቡ ፈሳሽ ዘይቶችን በድጎማ ከቀረጥ ነፃ ማስገባት እንደሚገባም አሳስቧል ኢንስቲትዩቱ። በተጨማሪም የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት አምራቾች ያለባቸውን ውስንነት አስተካክለው በተሻለ ጥራትና መጠን ማምረት እንዲችሉ መንግስት እገዛ ማድረግ እንዳለበት ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም