በሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤትና በተቃዋሚዎች መካከል ተቋርጦ የነበረውን ውይይት ለመቀጠል ሁለቱ አካላት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
በሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤትና በተቃዋሚዎች መካከል ተቋርጦ የነበረውን ውይይት ለመቀጠል ሁለቱ አካላት ተስማሙ
ሰኔ 5/2011 በኢትዮጵያ አደራዳሪነት በሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤትና በተቃዋሚዎች መካከል ተቋርጦ የነበረውን ውይይት ለመቀጠል ሁለቱ አካላት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ትናንት ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሰየሙት ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማህሙድ ድሪር በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሱዳን ለሚገኙ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ሁለቱን ወገኖች በማወያየት ከዚህ በፊት ተቋርጦ የነበረውን ውይይት ለማስቀጠል በአምስት ነጥቦች ዙሪያ መግባባት ላይ መደረሱንም ማስታወቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሁለቱ ወገኖች ድርድሩ ከመቋረጡ በፊት በሽግግር መንግስቱ አወቃቀር ስልጣን እና ሃላፊነት ዙሪያ ደርሰውበት የነበረውን ስምምነት ለማጽናት፣ የሉአላዊነት ምክር ቤት ምስረታ እና ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች ዙሪያ ልዩነቶችን ለማጥራት ውይይቱ እንዲቀጥልና ሁለቱ ወገኖች ጠብ አጫሪ መግለጫዎችን ከማውጣት እንዲታቀቡና ውጥረትን ለማርገብ እንዲሰሩ ተስማምተዋል። በተጨማሪም ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታትን ጨምሮ የመተማመን መንፈስ የሚያጠናክሩ እርምጃዎችን ለመውሰድ እና የነፃነትና ለውጥ ኃይሎች በበኩላቸው የህዝብ እምቢተኝነት ጥሪያቸውን ለመሰረዝ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አምባሳር ማህሙድ ድሪር ገልጸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራው የልዑካን ቡድን ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሌተናል ጀነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሀን ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው። በሱዳን በነበራቸው ቆይታ ባካሄዱት የማሸማገል ጥረት ጎን ለጎንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ከነጻነትና ለውጥ ኃይሎች አባላት ጋርም ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ ሌተናል ጀነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሀን ጋር በሱዳን ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ስለተጀመረው ሽምግልና ሂደት በስልክ መነጋገራቸውም የሚታወስ ነው። ውይይታቸው ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች እንዴት ይቀጥሉ በሚለው ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነና ሁለቱ ወገኖች አሁን ያለው ሁኔታ የተሻለ መፍትሄ እንደሚያገኝ ተስፋ እንዳላቸውም አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በወታደራዊ ምክር ሽግግር ቤትና በተቃዋሚዎች መካከል ተቋርጦ የነበረውን ውይይት ለማስቀጠልና ለማደራደር ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማህሙድ ድሪርን መሰየማቸውም አይዘነጋም።