ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተቀረጹ የሕዝብ ዘፈኖችና ውዝዋዜዎች ከሃንጋሪ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ ነው

ሰኔ 5/2011 ከ55 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተቀረጹ የሕዝብ ዘፈኖችና ውዝዋዜዎች ከነበሩበት ሃንጋሪ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ ነው።  የርክክብ ስነ ስርዓቱ በመጪው አርብ እንደሚካሄድም የብሄራዊ ቤተ መጻህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ከሃንጋሪ ኤምባሲ ጋር በሰጠው መግልጫ አስታውቋል። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሁለት የሃንጋሪ የኢትኖግራፊ ባለሙያዎች በ1965 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በስምንት ክልሎች የሕዝብ ሙዚቃዎችንና ውዝዋዜዎችን አሰባስበው ነበር። መረጃዎች እንደሚያሳዩት እነዚህ ባለሙያዎችን ለመሰብሰብ አራት ወራት የፈጀባቸው ሲሆን ደብረ ማርቆስ ፣ ጎንደር፣ ኮረም መቀሌና ጅማን በመሳሰሉ 13 ቦታዎች በመዘዋወር አሰባስበውም ነበር። ከአገር ውስጥም ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን ባካተተው እንቅስቃሴ ከ28 ያላነሱ የሙዚቃ አርቶችና 4 ሺህ ሜትርስ ፊልምና የአገሪቷን ትውፊቶች የሚያሳዩ ፎቶዎች እንደተሰበሰበ ለማወቅ ተችሏል። በኢትዮጵያ የሃንጋሪ ኤምባሲ ንግድና ኢኮኖሚ አታሼ  ዶከተር ባላዝ ዜሊንገር እንደተናገሩት፤ በወቅቱ የሙዚቃና የውዝዋዜ ስራዎችን ማሰባሰብ የተፈለገው የሁለቱ አገራት ኢትኖግራፊ ተመራማሪዎችና የታሪክ ምሁራን በጋራ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው በግዜው በተቀሰቀሰው አብዮት ምክንያት ሁሉም ነገር መረሳቱን ይገልጻሉ። የተሳበሰቡት የሕዝብ ሙዚቃዎችና ውዝዋዜዎች ለባህል፣ለሙዚቃና ጥናት ለሚያካሂዱ ሰዎች ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የሃንጋሪ መንግሥት ሥራዎችን ወደ ዲጂታል ቀይሮ ለኢትዮጵያ ለማስረከብ መወሰኑን ተናግረዋል። በዚህም መሰረት የስራዎቹን ስብስብ ለሚመለከታቸው አካላት የማስረከብ ስነ ስርዓት በቀጣዩ አርብ እንደሚካሄድ አመልክተዋል። የሃንጋሪ የማይዳሰሱ ቅርሶች ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ዶክተር ኢዝተር ሶንካ በበኩላቸው አገራቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንን እንደምታከብር ገልጸው ከኢትዮጵያ የተሰባሰቡ ቅርስችም በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ እንደሆነ አስረድተዋል። የሃንጋሪ መንግሥት ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራውን ሙሉ ወጪ መሸፈኑን ጠቅሰው አገራቱ በዚህ ላይ አብረው መስራታቸው ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክር እንደሆነም ጠቁመዋል። ወደ ዲጂታል የተቀየረው የሙዚቃና የውዝዋዜ ስብስብ በቀጣዩ አርብ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት፣ ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋምና ለብሄራዊ ቤተ-መጻህፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ  የማስረከብ ሥነ ስርዓት ይካሄዳል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በዚሁ ወቅት ''የሃንጋሪ መንግስት ስራዎችን ወደ ዲጂታል ቀይሮ ለእኛ በማስረከቡ ሊመሰገን ይገባል'' ያሉ ሲሆን ጥናትና ምርመር አድራጊዎች፣የሙዚቃ ባለሙያዎችና ማንኛውም ፍላጎቱ ያለው ሰው እንዲጠቀምበትም ክፍት ይደረጋል ብለዋል። ''በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መጻሕፍትን ጨምሮ በርካታ ቅርሶች በተለያዩ አገራት ይገኛሉ'' ያሉት ዳይሬክተሩ ሃንጋሪ እነዚህን የሙዚቃና የውስዋዜ ስብስቦች ለኢትዮጵያ መመለሷ ለሌሎች አገራትም ትልቅ ምሳሌ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ሰላማዊት አራጋው በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ስብስቡን ለመማር ማስተማር ሂደቱ በግብዓትነት እንደሚጠቀምበት ጠቁመዋል። ጥናት ለሚሰሩ ተማሪዎችም ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ ይመቻቻል ሲሉም አክለዋል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም