ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዕርቅ ኮሚሽን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ኬንያ ይገኛል

ሰኔ 3/2011  የብሄራዊ የእርቅ ኮሚሽን አባላት ያሉበት ቡድን ከሰኔ 3 እስከ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ልምድ ለመቅሰም ኬንያ መግባቱ ተገልጿል። በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ቡድኑ በናይሮቢ ቆይታው በኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ የተካሄዱ የሃቅ እና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችል የልምድ ልውውጥ ያደርጋል። በተጨማሪም በኬንያ የብሄራዊ የአንድነት ኮሚሽን አስራር፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ለሰላም ግንባታ በሚኖራቸው ሚና ላይ የቡድን አባላቱ ስልጠና እንደሚወስዱ የኤምባሲው መረጃ አመልክቷል። ጉብኝቱን በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገ በሰላም ግንባታ ላይ የተሰማራ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዕርቅ ኮሚሽን የተለያየ አቋም የያዙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየትና ለሃገራዊ እርቅ መሰረት የሚሆኑ የጋራ መርህዎችንና እሴቶችን መለየትን ጨምሮ የተለያዩ ሃላፊነቶች የተሰጠው ነው። የግጭቶችንና የመብት ጥሰቶቹን መነሻ ምክንያት ለመለየት፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውዶችን፣ የተጎጂዎችንና ጥፋተኞቸን አስተያየት በመወሰድ የማጣራት ስራ ማካሄድም በአዋጅ የተሰጠው ስልጣን ነው። ኮሚሽኑ ሀላፊነቱን ለመወጣት የማናቸውንም ተቋም ይዞታ የመጎብኘት፣ በጉብኝቱም ጊዜ የሚያገኛቸውን ማናቸውንም መረጃዎችና፣ ሰነዶችን ቅጂ የመውስድ፤ መረጃ ለመሰብሰብ በተናጠልም ሆነ በቡድን፣ በሚስጥርም ሆነ ለህዝብ ክፍት በሆነ ሁኔታ ቃለ መጠይቅ ማድረግ፣ መጥሪያ በመላክ ማንኛዉም ሰው እንዲቀርብ የማዘዝ እና ቃሉን በቃለ መሃላ እንዲሰጥ የማድረግ ስልጣን አለው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም