''ከኩረጃ የነፃ የተማረ ትውልድ መፍጠር ለምንገነባት ታላቅ አገር ምሰሶ ይሆናል''-የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ ማሃዲ ጊሬ - ኢዜአ አማርኛ
''ከኩረጃ የነፃ የተማረ ትውልድ መፍጠር ለምንገነባት ታላቅ አገር ምሰሶ ይሆናል''-የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ ማሃዲ ጊሬ
ድሬዳዋ ሰኔ 3/ 2011ከኩረጃ የነፃ የተማረ ትውልድ መፍጠር የምንፈልጋትን ታላቅ አገር ለመገንባት መሠረት ይሆናል ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ተናገሩ፡፡ ምክትል ከንቲባው በድሬዳዋ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተገኝተው የ10ኛ ክፍል ፈተናን አስጀምረዋል። ለተማሪዎችም መልካም ፈተናና የፈተና ጊዜ ተመኝተዋል፡፡ ኩረጃን ለማስቀረት የተቀናጀ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተካተቱበትና የአስተዳደሩ አመራሮች ያሉበት ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን አስታውቀዋል። በዚህም በተለያዩ መንገዶች የሚካሄደውን የፈተና ስርቆትና ኩረጃ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ''እኔም በዚህ ትምህርት ቤት ነበር የተማርሁት። በወቅቱ ኩረጃ አናውቅም።የአሁኑ ትውልድ ከእኛ መልካሙን መቅሰምና ኩረጃን መጠየፍ አለበት'' ብለዋል፡፡ የዛሬ ተማሪ ባለው ብቃትና ችሎታ ነው ለዚህች አገር የሚጠቅመው ያሉት አቶ መሃዲ፣ ይህን መረዳትና በራሳቸው ተማምነው የሚጣልባቸውን የፈተናም ሆነ ሌሎች ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ ነገ እንድትፈጠር የምናስባትን ታላቅ አገር ተረካቢና ገንቢዎች የዛሬዎቹ ተማሪዎች በመሆናቸው በራሳቸው የሚተማመኑ ዜጎች እንዲሆኑ ሁላችንም ልናግዛቸው፣ ልንገራቸው ይገባል በማለትም ተናግረዋል፡፡ በዚህ መንገድ መጓዝ ከተቻለ ነገ እንድትኖረን የምንፈልጋትን ታላቅ አገር ለመገንባት መንገዱ የተደላደለ ይሆናል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ኩረጃ ራስን የሚያጠፋ ህመም መሆኑን በመረዳትና ኩረጃን በመጠየፍ ተማሪዎች ባላቸው ችሎታ ፈተናቸውን እንዲፈተኑ አሳስበዋል፡ለተከታዮቻቸውም ፈተናውን በድል በማጠናቀቅ አርአያ መሆኑን እንዳለባቸው ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል፡፡ የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ ፈተናው ያለ ምንም ችግር ለማካሄድ ወላጆች ፣ መምህራን ማህበር፣ የማህበረሰቡ ተወካዮች፣ የትምህርትና የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች በራሳቸው የሚተማመኑ ዜጎች እንዲሆኑ በአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ትምህርት መሰጠቱን ገልጸዋል። የመጀመሪያው የፈተና ቀን ሂደት በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ የፈተናው ሂደት የሚከታተሉት የድሬዳዋ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበበ ታምራት በ12 የገጠርና የከተማ የፈተና ጣቢያዎች 417 መምህራን ጨምሮ የፈተና ተቆጣጣሪዎች በፈተናው በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለፁት ተፈታኞች የቋንቋዎቹ ፈተናዎች ጥሩ መሆናቸውንና የሂሳብ ፈተና ግን እንደከበዳቸው ተናግረዋል፡፡ ተማሪ ሐጂ አህመድ የአፋን ኦሮሞ ፈተና በአፍ መፍቻዬ ቋንቋ የተዘጋጀ በመሆኑ ቀሎኛል፤ እንግሊዘኛም ጥሩ ነው ብሏል፡፡ የሂሳብ ፈተና ግን ከብዶኛል ብሏል። ተማሪ ኤደን አያሌው በበኩሏየሂሳብ ትምህርት ቀዳሚ ምርጫዋ በመሆኑ ከቋንቋዎቹ ፈተናዎች ይልቅ፤ ፈተናው እንደቀለላት ተናግራለች፡፡ በአስተዳደሩ 13ሺ 400 የሚጠጉ ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡