ቀጥታ፡

ስለአክሬዲቴሽን ግንዛቤ በማዳበር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2011 የንግድ ዘርፍ የመንግስት ተቆጣጣሪ አካላትና ሸማቾች ማሕበራት ስለአክሬዲቴሽን ግንዛቤ አዳብረው ከአቅርቦት ትስስሩ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ተጠየቀ። በአገራችን ለ9ኛ ጊዜ የአለም አክሬዲቴሽን ቀንን “አክሬዲቴሽን ለአቅርቦት ትስስር እሴት ይጨምራል” በሚል የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር አክብሯል። አክሬዲቴሽን ምርትና አገልገሎትን በተቀመጡ ደረጃዎች፣ ስነ-ልክና በተስማሚነት ምዘና የመፈተሽና አገልግሎት ላይ የማዋል ስርዓት ነው። የአክሬዲቴሽን አገልግሎት በአገር ውስጥ የተሰጠበትን ምክንያት የገለፁት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ዜጎችን በ3ኛ ወገን ብቃታቸው በተመሰከረላቸውና “አክሬዲትድ” የሆኑ ተቋማትን እንዲጠቀሙ ለማስቻል ያለመ ስራ እየተሰራ ነው። ይህም የፍተሻ ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ተቀባይነትና ተዓማኒነትን ያካትታል ብለዋል። ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ዘርፉ ሁሉንም አገልግሎት ሰጭ እንደሚመለከትና ማንኛውንም ምርትና አገልግሎት በሚፈለገው የአቅርቦት መጠንና ጊዜ ለማድረስ የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ መሆንን እንደመፍትሔ አመላክተዋል። የኢንስፔክሽን፣ የሰርተፊኬሽን ተቋማትንና የላቦራቶሪ አገልግሎት መስጫዎችን ስራቸውን ለህብረተሰቡ እየሰጡ ካሉት አገልግሎት አንጻር እንዲያዩትና ያሉበትን ደረጃ በመስፈርቱ ፈትሸው ግብረ-መልስ ለጽሕፈት ቤቱ እንዲያቀርቡ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እሸቴ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳርክተር አቶ አርዓያ ፍሰሃ በበኩላቸው በአገሪቱ በአክሬዲቴሽን የተሻለ ትስስር ለመፍጠርና ህብረተሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ጽሕፈት ቤቱ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የስልጠና ማዕከላትንና የቢሮ ግንባታዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም በውጤታማ ዋጋ፣ ጥራት እንዲሁም ውስብስብ የአቅርቦት ትስስርን በበርካታ ሴክተሮች በማቋረጥ አዳዲስ መዳረሻዎችን ለማፍራትም መስራቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤትም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፉ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ለፍተሻና፣ የህክምና ላቦራቶሪዎች ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ተቋማት የአክሬዲቴሽን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። የኢትዮጵያ ምዘና ኤጀንሲዎች፣ ከኢትዮጵያ ተስማሚነትና ደረጃዎች ኤጀንሲ እና ከሚኒስቴር ተቋማት አስፈጻሚዎች በዝግጅቱ ላይ ታድመዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘውን ደረጃ መሠረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማት ዓለም አቀፍ የአክሬዲቴሽን ፎረምና ዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ አክሬዲቴሽን ትብብር አካላት ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም