በጭሮ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ አለመወገድ ለጤና ችግር እያጋለጠን ነው - ነዋሪዎች

65
ጭሮ  ሰኔ 1/2010 ከጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚወጣው ፍሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ ባለመወገዱ ለጤና ችግር  እያጋለጠን ነው ሲሉ የጭሮ ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ገለፁ፡፡ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት ከተለያዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚወጣው ፍሳሽ ቆሻሻ በጤንነታቸውና በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ። ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጄይላን አህመድ በሰጡት አስተያየት “ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች በሚወጣው ፍሳሽ ቆሻሻ ምክንያት ልጆቻችን በየጊዜው  እየታመሙብን ነው “ ብለዋል። በአካባቢው በሚፈጠረው መጥፎ ሽታ በአካባቢው ለመኖር እየተቸገርን ነው፤ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ለከፋ የጤና ችግር ልንጋለጥ እንችላለን የሚል ስጋት እንዳለባቸው የገለፁት ደግሞ የከተማው ነዋሪ  ወይዘሮ ሀና ደምሴ ናቸው፡፡ ''ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጊዜ ለከተማው አስተዳድር አቤቱታ ብናሰማም እስካሁን መፍትሔ አላገኘንም'' ሲሉም ቅሬታቸውን ገልፀዋል ። ወይዘሮ አሽረቃ መሀመድ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው  በግድየለሽነት የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ አካባቢያቸውን እየበከለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከእነልጆቻቸው ለበሽታ እየተጋለጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ምንም አይነት የደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ አለማዘጋጀቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እንዲባባስ እንዳደረገው አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዲንቅሳ ደበላ የተባሉ የከተማው የሀገር ሽማግሌ በበኩላቸው  መስተዳድሩ የቆሻሻ መጣያ ቦታዎች አለማዘጋጀቱ እንዳለ ሆኖ  የህብረተሰቡ አካባቢን የማጽዳት ባህል  ዝቅተኛ መሆን ችግሩ እንዲባባስ እንዳደረገው ተናግረዋል። የከተማው ነዋሪ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ሲገባው በግድየለሽነት በየቦታው መጣል ተመልሶ እራሱን እንደሚጎዳ ተገንዝቦ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሀገር ሽማግሌው መክረዋል ። የጭሮ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የጽዳትና ውበት ሥራ ሂደት መሪ አቶ ነስረዲን ኡስማኢል ከቢራ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ህዝቡ ያነሳው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አምነው ከዚህ በፊት የነበረው የቆሻሻ ማስወገጃ ጉድጓድ በቂ ባለመሆኑ ችግሩ እንደተፈጠረ ተናግረዋል፡፡ አዲስ የቆሻሻ ማስወገጃ ጉድጓድ ለማሰራት የዲዛይን ስራው ተጠናቆ ወደ ስራ ለመግባት የበጀት ችግር ማነቆ ሆኖ እንደቆየ  ገልጸዋል፡፡ አሁን ግን የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በመጪው አዲስ የበጀት ዓመት የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ለመገንባት መታሰቡን አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም