አብን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል የሚዛወሩበት ጊዜው አሁን አለመሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አብን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል የሚዛወሩበት ጊዜው አሁን አለመሆኑን ገለጸ
ሰኔ 3/2011 የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ ከመዛወራቸው በፊት ድርጅቶቹ የተሰማሩበትን ዘርፍ ለውድድር ክፍት ማድረግ እንደሚገባ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ገለጸ። ኢህአዴግ አገር የሚመራበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስር ነቀል በሆነ መልኩ መለወጥ የሚችለው አዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለምርጫ ውድድር አቅርቦ የህዝብ ፈቃድና ይሁንታን ሲያገኝ ብቻ መሆኑን ገልጿል። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ በመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የፓርቲው ኢኮኖሚ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ካሱ ሀይሉ እንዳሉት፤ አሁን የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ማዞሩ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። መንግስት የኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮጰያ አየር መንገድን ወቅቱን ባልጠበቀ ሁኔታ ለግል ባለኃብቶች ለማስተላለፍ የደረሰበት ውሳኔ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ያሳጣልም ብለዋል። በህግ በብቸኝነት የመነገድና አገልግሎት የመስጠት መብት የተሰጣቸውን ተቋማት በከፊልም ይሁን ሙሉ በሙሉ ወደግል ይዞታ ማዞር "ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ" ውሳኔ ነው ብለዋል። ኢትዮ-ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊልም ይሁን በሙሉ ወደ ግል ከማዞሩ አስቀድሞ ድርጅቶቹን ለውድድር ክፍት ማድረግ ይኖርበታልም ብለዋል በመግለጫው። አሰራሮች ለሙስና እና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ በመሆኑ ለመሰረታዊ ማህበራዊ ልማት ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ወለድ የተበደረው የውጭ ዕዳ የሀገሪቱን አጠቃላይ ምርት 60 በመቶ ድርሻ ይይዛል። መንግስት ጠንካራ ተፎካካሪ አገልግሎት ሰጭ የንግድ ተቋማት ሳይገነባና ዘርፉን የማስተዳደር የመምራት አቅም ሳያፈጥር ፈርጣማ የግል ድርጅቶችን መቆጣጠር አይችልም ብለዋል። በመሆኑም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ከማዛወሩ በፊት በቅድሚያ ድርጅቶቹ የተሰማሩበትን ዘርፍ ለውድድር ክፍት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። አብን ከኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጋር ባደረገው ጥናት በአሁኑ ወቅት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ማዛወር የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዳ ነው። የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መልካሙ ሹምዬ በበኩላቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በተመለከተ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ የሚችለው የህዝብን ይሁንታና ፈቃድ ሲያገኝ ብቻ ነው ብለዋል። "በአብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ መንግስት በህዝብ ተመርጫለሁ" የሚለው ኢህአዴግ አዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መቀየር የሚችለው በምርጫ የህዝብ ፈቃድ ሲሰጠው መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ኩራት የሆነውንና እንከን የማይወጣለትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ግል ለማዛወር አስገዳጅ ምክንያት የለውም ብለዋል። ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎችን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ከመዞራቸው በፊት መንግስት ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበት ፓርቲው በሰጠው መግለጫ አሳስቧል።