በጋምቤላ ክልል የ10ኛ ክፍል ፈተና ለሌሎች ሊፈተኑ የሞከሩ ሰዎች ተያዙ

85
ጋምቤላ ሰኔ 3 / 2011 በጋምቤላ ክልል የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለሌሎች ለመፈተን የሞከሩ ሁለት ግለሰቦች መያዛቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቶማስ የማሎ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ለሌሎች ፈተና ለመፈተን  ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት በዲማና በኮርገንግ ከተሞች በተቋቋሙ ፈተና ጣቢያዎች ነው። በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ጉዳይ ለፍርድ እንደሚቀርብም አስረድተዋል። ከዚህ ውጭ  በአንዳንድ ጣቢያዎች የፈተና መረካከቢያ ቅጽ እጥረት ገጥሞት እልባት እንዲያገኝ ማድረጉን ገልጸዋል። ፈተናው በተቃና መልኩ እንዲካሄድ ከክልል እስከ ፈተና ጣቢያ ድረስ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በተደራጀ  ሁኔታ ሂደቱን  እየተከታተለ ነው ብለዋል፡፡ በጋምቤላ ከተማ ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል  ተማሪ ቤኒ ዱላ በሰጠችው አስተያየት ፈተናውን  ያለምንም ችግር መውሰዷንና ተማሪዎችም በራስ መተማመን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡ ፈተናውን ያለምንም ችግር እንደወሰደና በዚህ መልኩ መቀጠል እንደሚገባው የተናገረው ደግሞ ተማሪ ዳዊት  ሳዶም ነው፡፡ በክልሉ 13 ሺህ 270 ተማሪዎች በ52 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናውን እየወሰዱ መሆናቸውን የቢሮው መረጃ  ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም