የኢትዮጵያ ቢዝነስ ሩጫ ሰኔ 30 ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቢዝነስ ሩጫ ሰኔ 30 ይካሄዳል
ሰኔ 3/2011 ሶስተኛው የአምስት ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያ የቢዝነስ ሩጫ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል። የጎዳና ሩጫ ውድድሩ "ለኢንዱስትሪ ልማት እንሩጥ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ውድድሩ መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ የሚያደርግ ሲሆን፤ ከአምስት ሺህ በላይ የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች እና ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የውድድሩ ዓላማም በአገሪቷ የሚገኙ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ እና በኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ እንዲጎለብት የማስተዋዋቅ ስራ እንደሆነ ምክር ቤቱ በላከው መግለጻ አመልክቷል። በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ባለሀብቶች የተሰማሩት በአገልግሎት ዘርፍ እንደሆነ የጠቆመው መግለጫው፤ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ልማት ያላቸውን ተሳትፎ ቢያሳድጉ ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ስለሚችሉ በዘርፉ እንዲሳተፉ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። በኢትዮጵያ ያለውን የስራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ሚና ወሳኝ እንደሆነ መሆኑን ጠቁሞ፤ ለዚሁ ጉዳይ ባለሀብቶችም ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ገልጿል። መንግስትም ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ የቅስቀሳና የማስተዋወቅ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበትም በመግለጫው ተጠቅሷል። በተጨማሪም የውድድሩ ተሳታፊዎች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ በመሳተፍ ጤንነታቻውን እንዲጠብቁ ማድረግ የሩጫው ሌላኛው አላማ እንደሆነም በመግለጫው ተመልክቷል። በመጀመሪያው የቢዝነስ ሩጫ ሁለት ሺ በሁለተኛው ሶስት ሺህ ተሳታፊዎች እንደተካፈሉም ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዚህ ሩጫ ላይ ባለሀብቶችና ሠራተኞቻቸው፣ አርቲስቶችና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።