ቀጥታ፡

የህንዳዊያን የስነ ህንጻ ጠቢባን አሻራ ያረፈባቸው የአዲስ አበባ ህንጻዎች ተጎበኙ

ሰኔ 3/2011 አዲስ አበባ ስትመሰረት ጀምሮ በሕንዳዊያን የስነ ህንጻ ጠቢባን የተነጹ የአራዳ አካባቢ ህንጻዎች ተጎበኙ። የታላቁን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማህተመ ጋንዲን ልደት ምክንያት በማድረግ የተደረገው የእግር ጉዞው መነሻና መድረሻውን ከእቴጌ ጣይቱ ሆቴል በማድረግ ትናነት ማምሻውን ተካሂዷል። በጉብኝቱ በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲና በአፍሪካ ህብረት የህንድ አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫን ጨምሮ የኢምባሲው ሰራተኞችና ልዩ ልዩ የውጭ አገራት ዜጎች ተሳትፈዋል። ጉብኝቱ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ከሆነው ከእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ጀምሮ በሲኒማ ኢትዮጵያ-በአራዳ ህንጻ፣ በቸርችል ቪው አደባባይ- አራዳ ፖስታ ቤት- የሩስያ ባህል ማዕከል- በካቶሊ ካቴድራል-ኤልያና ሆቴል-በባንኮ ዲሮማ ህንጻ በመዞር በማህተመ ጋንዲ ጎዳና ጣይቱ ሆቴል ተጠናቋል። በጉበኝቱ በህንዳዊያን ባለሙያዎች ተሰርተው ዛሬ ላይ በመኖሪያ ቤት፣ በንግድና በመንግስት  ተቋማትነት እያገለገሉ የሚገኙ በርካታ ታሪካዊ ህንጻዎች ተጎብኝተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ተቋም ተባባሪፕሮፌሰር አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ እንዳሉት የአዲስ አበባ ከተማ ቀዳሚው የንግድና የገበያ ማዕከል የነበረው የቀድሞው አራዳ የዛሬው ፒያሳ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነው። በርካታ ህንዳዊያን ነጋዴዎችና የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ከከተማዋ ምስረታ ጀምሮ እንደነበሩ  ገልጸው፤ ታዋቂው ህንዳዊ የኪነ ህንጻ ባለሙያ ሃጂ ቀዋስ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጥሪ በርካታ ህንጻዎችን መስራታቸውንም ተናግረዋል። ህንዳዊያን የስነ ህንጻ ጠቢባን በእንጨት፣ በጭቃና በጥርብ ድንጋይ የቤት አሰራር ጥበባቸው አዲስ አበበ ላይ ታሪካዊ አሻራ ማሳረፋቸውን ገልጸው፤ በተለያዬ ምክንያት የተወሰኑት ቢፈረሱም ዛሬም ለአዲስ አበባ ከተማ ማንነት ታሪክ ሊዘክሩ የሚችሉ ግንባታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። በወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ያሰሯችውንህንጻዎች በመመልከት በርካታ መኳንንት የህንድ የስነ ህንጻ ጠቢባንን የመኖሪያ ቤትና የንግድ ተቋማትን ማሰራታቸውም ታውቋል። በአራዳ ኣካባቢ ከሚገኙ ጥንታዊ ህንጻዎች ባሻገር ግቢ ገብርኤል፣ የዳግማዊ ምኒልክ የግብር አዳራሽ፣ የእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ የቀድሞው የራስ ብሩ መኖሪያ በት የዛሬው የአዲስ አበባ ቤተ መዘክር የህንዳዊያን አሻራ ያረፈባቸው ታሪካዊ ቅርሶች መሆናቸውም ተገልጿል። ጥንታዊ ታሪካዊ ህንጻዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ ቅርሶች በመሆናቸው ካላቸው ታሪካዊናማኅበረሰባዊ ፋይዳ አንጻር ቅርሶችን መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡ ታሪካዊ ሕንፃዎች ሲፈርሱ የማኅበረሰቡ የቀደመ ታሪክ ከመሸርሸሩ ባሻገር በቱሪዝም ረገድ የሚገኘው ጥቅምን እንደሚያሳጣም ተናግረዋል። አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫን ህንጻዎችን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የቀድሞዋ አዲስ አበባ የህንጻ አሰራር ጥበቦች የሀንድ ዜጎች የስነ ህንጻ ባለሙያዎች ተጽዕኖ እንዳለባቸው አረጋግጠዋል። በተለይም በፒያሳ ኣካባቢ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተጋበዙ የስነ ህንጻ ሙያተኞችና ግንበኞች ያሳረፉት ትልቅ አሻራ በጉልህ ታትሞ ዛሬም በአዲስ  አበባ ይታያል ነው ያሉት። 'ህንጻዎቹ የጋራ የስነ ህንጻ ቅርሶች ናቸው' ያሉት አምባሳደሩ፣ በቅርሶች ታሪካዊ ፋይዳ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ህንጻዎቹን ማደስና መጠበቅ የሁላችንም ሃላፊነት በመሆኑ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድርና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ኤምባሲው ቅርሶቹ እንዲጠበቁና እንዲታደሱ ጥረት ያደርጋል ነው ያሉት። ከ2000 ዓመታት በፊት በኢ-መደበኛነት የተጀመረው የኢትዮ ህንድ ታሪካዊና የባህል ቁርኝት ዛሬ ላይ በቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ጉልህ እምርታ ማምጣቱን አምባሳደሩ ተናገረዋል። በትምህርት፣ በሲኒማ፣ በሙዚቃና ቋንቋ ያለው የሁለትዮሽ ባህላዊ ትስስር የሁለቱን አገራት ዜጎች ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲዳብር ማድረጉንም ገልጸዋል። ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም በሃይል፣ በስኳር ልማት፣ በሰው ሃይል አቅም ግንባታ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በፈጠራና ቴክኖሎጂ መስኮች ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም