ቀጥታ፡

የግእዝ የስነ ፈውስ መጻህፍት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የግእዝ ቋንቋን ማስረጽ ይገባል

ግንቦት 3/2011 ጥንታዊያን የግእዝ የስነ ፈውስ መጻህፍት ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲውሉ የግእዝ ቋንቋን ማስረጽ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ። በመቐሌ ዩኒቨርሲቲ " ግእዝና ስነ-ፈውስ " በሚል ርዕስ የተዘጋጀው አምስተኛው አገር አቀፍ የግእዝ ጉባኤ ተካሂዷል ። በጉባኤው ላይ የተገኙት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንዳያ ገብረህይወት አገር በቀል እውቀት የአገር እድገት እንደሚያመጣ ተናግረዋል። በመሆኑም በብራና የግእዝ መጻህፍት ላይ ሰፍረው የሚገኙ የአገር በቀል እውቀቶችን በማጥናትና በመሰነድ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በቀመራዊ ስነ-ልሳን የበለፀገ፣ ፊደል የተቀረፀለትና በአፍሪካ የራሱ የአፃፃፍ ስርአት ያለው ብቸኛ የግእዝ ቋንቋ ባለቤት በመሆኗ ሊያኮራና ሊጠበቅ እንደሚገባም ገልፀዋል። “ግእዝ የእድገታችን ምስክርና የአገር በቀል እውቀታችን ምንጭ ነው” ያሉት ፕሮፌሰር ክንዳያ በአገሪቱ የሚገኙ የብራና የግእዝ መጻህፍት ግብረገብነት፣ ታሪክ ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ ስነ-ኮዋክብትና ስነ-ፈውስ ይዘት እንዳላቸው አስረድተዋል። አገር በቀል እውቀት የማይቀለበስ የአገር እድገት እንደሚያመጣ ገልጸው፣ “በብራና የግዕዝ መፃህፍት ላይ ሰፍረው የሚገኙ አገር በቀል እውቀቶች እንዲጠኑና እንዲሰነዱ እንድህ አይነት መድረክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል” ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው በቅዱስ ያሬድ የጥንታዊ ፅሁፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የጀመራቸው የብራና ጥናቶችን አጠናክሮ በመቀጠል ለህብረተሰቡ ጠቀሜታ እንዲውሉ እየሰራ መሆኑንም ፕሮፌሰር ክንዳያ አያይዘው ገልጸዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው “ለግእዝ ቋንቋ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሰነድ ለትውልድ ለማስተላለፍ ጠንክሮ መስራት ይጠበቃል” ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለፉት የግእዝ ጉባኤዎችን በመገምገም በቋንቋው ላይ የተካሄዱ ጥናቶች ውጤታማ እንደነበሩ ማረጋገጡን ጠቁመዋል። አምስተኛው የግእዝ ጉባኤ በስነ-ፈውስ ላይ ትኩረት በማድረጉ ለየት እንደሚያደርገው የገለጹት ወይዘሮ ብዙነሽ፣ የግእዝ ጥንታዊያን መጻህፍት ለህክምና ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ ታላላቅ አባቶች እንደዛሬ ዘመናዊ ህክምና ባልተስፋፋበት ወቅት የኢትዮጵያን ህዝብ አክመውና ጤናውን ተንከባክበው ጤናማ ትውልድ ማስረከብ የቻሉት በስነ-ፈውስ ላይ በተፃፉ ጥንታዊያን የብራና መጻህፍት አማካኝነት ነው። በዚህም በህክምና ዙሪያ የተፃፉ የግእዝ ጥንታዊያን መጻህፍት በጥናትና ምርምር በመለየት ከዘመናዊው የህክምና እውቀት ጋር በማጣጠም ለህዝብ ጥቅም እንዲውሉ ጉባኤው ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በግእዝ ቋንቋ ላይ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ የመንግስትና የግል ተቋማት ከጎናቸው ሆኖ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። "ኢትዮጵያውያን ከታመመ የታሪክ ግንዛቤያችን ለመፈወስ በግእዝ ቋንቋ የተፃፉ ጥንታዊያን መጻህፍትን ማወቅና መተርጎም ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ናቸው ። “በውጭ የታሪክ ፀሐፊዎች እየተፃፉ ያሉ የኢትዮጵያ የታሪክ መጻህፍት ከጥንታዊያን የግእዝ መፃህፍት የሚወሰዱ ቢሆኑም ግዕዝን በጥልቀት ካለማወቅና ከመተርጎም ማነስ የተነሳ ታሪክችን እየተዛባና እየጠፋ ይገኛል” ሲሉም ገልጸዋል። በመሆኑም ከተዛባ ታሪክ ለመውጣት የኢትዮጵያ የታሪክ ፀሐፊዎች ከጥንታዊያን የግእዝ መፃህፍት ተነስተው እንዲነሱ የግእዝ ቋንቋን ማወቅና መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። “የግእዝ ቋንቋ የሃይማኖታዊ ቋንቋ ነው የሚል አስተሳሰብን በመስበር እንደማንኛውም ቋንቋ የማህበረሰቡ አማራጭ ቋንቋ ሆኖ እንዲቀጥል እንቅስቀሴ ተጀምሯል” ያሉት ደግሞ የቅዱስ ኤፍረምናጦስ አቡነ ሰላማ ክሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን መጋቤ ብርሃናት ተስፋይ አደራ ናቸው ። የግእዝ ቋንቋ ከቤተ ክርስቲያን ወጥቶ ለህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ቋንቋ መግባቢያ ሆኖ እንዲያገለግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና መንፈሳዊ ኮሌጆች የጀመሩት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። በጉባኤው "ግእዝ ለስነ-ፈውስና ግእዝና የባህል መድኃንት" የሚሉ ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደረጎባቸዋል ። ጉባኤው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ ቤተመጻህፍትና ቤተ መዛግት ኤጀንሲ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው ። ከዚህ በፊት የግእዝ ቋንቋ ጉባኤ በአክሱም፣ በባህር ዳር፣ በጅማና በውልቅጤ ዩኒቨርሲቲዎች መካሄዱ ይታወሳል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም