በሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤና ጎንደር ከተማ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤና ጎንደር ከተማ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማሉ
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 በበዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማና ጎንደር ከተማ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ይጫወታሉ። አራት ቡድኖች በሚሳተፉበት የሊጉ ውድድር ነገ ከሚካሄደው ጨዋታ በስተቀር ሁሉም መርሃ-ግብሮች ፍጻሜ አግኝተዋል። ወልቂጤ ከተማ ከጎንደር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ የሊጉን አሸናፊ የሚለይ ይሆናል። ሁለቱን ቡድኖች ተመሳሳይ ዘጠኝ ነጥብ ያላቸው ሲሆን የነገውን ጨዋታ ያሸነፈ ቡድን የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑን ያረጋግጣል። በመጀመሪያው ዙር ጎንደር ላይ በተደረገ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ጎንደር ከተማን ማሸነፉ የሚታወስ ነው። የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል። ስምንት ቡድኖች የሚሳተፉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየምና ወልቂጤ ላይ ይካሄዳሉ። የአንድ ሳምንት መርሃ ግብር የሚቀረውን የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤ ከተማ በ24 ነጥብ ሲመራ፣ ሃዋሳ ከተማ በ23 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት በ20 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ድሬዳዋ ከተማ 13 ነጥብ በመሰብሰብ የመጨረሻው ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በሌላ በኩል ወላይታ ድቻ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በቀጣዮቹ ቀናት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በዚሁ መሰረት እሁድ ከረፋዱ አራት ሰአት በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም አዲስ አበባ ፖሊስ ከሙገር ሲሚንቶ ይጫወታል። በክልል ከተማ ባህርዳር ላይ ጣናባህርዳር ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሚጫወቱ ሲሆን ሰኞ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት መከላከያ ከፌዴራል ማረሚያ የሚጫወቱ ይሆናል። የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ.ም ሶዶ ላይ ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በሚያደርገው ጨዋታ ዋንጫውን ይቀበላል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።