ቀጥታ፡

በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ወሰን ላይ በ832 ሚሊዮን ብር የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ

ሰኔ 2/2011 በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አጎራባች ወሰን ላይ የሚገኙ ህዝቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ በ832 ሚሊዮን ብር የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የሁለቱ ክልል የሰላምና የልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለጸ። ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ዛሬ በአዳማ  ከተማ  ገምግሟል። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሾመ ደሳለኝ እንዳሉት በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ወሰን ላይ የሚገኙ ህዝቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ በ832 ሚሊዮን ብር የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። “እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች መካከል መንገድ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ የመስኖ ልማትና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል” ብለዋል። አቶ ተሾመ እንዳሉት መሰረተ ልማቱ በምዕራብ ኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ ዞንና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን የሚገኙ ህዝቦችን በጋራ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግና የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው። በእዚህም እየተገባደደ ባለው የ2011 በጀት ዓመት የአካባቢውን ሰላም የማስፈንና የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። ለእዚህም የህዝቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በ392 ሚሊዮን ብር የገጠር መንገድ ግንባታና ደረጃን የማሳደግ ሥራ፣ የጤና ኬላዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ቁፋሮና የመስኖ ልማት ሥራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል። ህብረተሰቡ በተቀናጀ መልኩ ሰላሙን እንዲጠብቅ በምስራቅ፣ ምዕራብና ቄሌም ወለጋ ዞኖችና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች የሰላምና የልማት ኮንፈረንሶች እስከ ቀበሌ ድረስ መካሄዳቸውንም አቶ ተሾመ ተናግረዋል። በዚህም ከሁለቱ ክልል በወቅታዊ የፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ነበሩበት ቄያቸው ለመመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል። እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ ሥራቸው እየተከናወነ ያሉትንና አዳዲስ የሚጀመሩትን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ 440 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል። የፕሮጀክቱ ምክትል ኃላፊና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተወካይ አቶ ኮማንደር ወርቁ በባኩላቸው “ በአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት በዘላቂነት በማረጋገጥ ሰላምን ለማስፈን በሙሉ አቅም እየተሰራ ነው”  ብለዋል። ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች 162 ቀበሌዎችን እንደሚዋሰኑ ገልጸው፣ በሁሉም ቀበሌዎች ላይ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የህዝቦችን የጋራ ፍላጎት መሰረት ያደረገ ልማት ለማከናነወን በአሶሳና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች አማካይነት የዳሰሰ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል። “በዚህም በህዝቡ ቅድሚያ በተሰጣቸው የውሃ፣ መስኖ፣ ጤና፣ መንገድና ትምህርት መስኮች ግንባታ ለማከናወን በዩኒቨርሲቲዎቹ የዲዛይን ጥናት ተጠናቆ የግንባታ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነን” ብልዋል። “የጋምቤላና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ህዝቦችን በልማት ለማስተሳሰር ለቀጣዩ አምስት ዓመት የሚቆይ ስትራቴጅክ ዕቅድ እያዘጋጀን ነው” ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ክልል የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አርታ ሙስጠፋ ናቸው። የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ የጋራ ተጠቃሚነትና ልማት ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ገልጸው፣ የጋምቤላ ክልል በልማት እቅድ ዝግጅት፣ በአቅም ግንባታና በሰው ኃይል ልማት ዙሪያ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመልክትዋል። በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቴ በባኩላቸው የኦሮሚያ ክልል ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ሰላም፣ ልማትና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ስትራቴጂክ ዕቅድ ወጥቶ ወደ ተጨባጭ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል። ከጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጋር ጠንካራ የልማትና የጋራ ተጠቃሚነት ትስስር ለመፍጠር የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በአዳማ ከተማ ዛሬ በተካሄደው መድረክ ላይ ከጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም