ቀጥታ፡

ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በማሸነፍ ጉዞው እንደቀጠለ ነው

ሰኔ 2/2011 ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊነቱን አስቀጥሏል። በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ትናንት ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል። ጎንደር ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጎንደር ከተማን 37 ለ 23 አሸንፏል። ውጤቱንም ተከትሎ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ በሊጉ በጣም ውጤታማ ጉዞ እያደረገ ይገኛል። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታም የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከምባታ ዱራሜን 42 ለ 27  አሸንፏል። በ17ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በፎርፌ ውጤት ተጠናቀዋል። መከላከያ ከቡታጅራ ከተማ በዚህ ሳምንት ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው። ነገር ግን ቡታጅራ ከተማ በጨዋታ ሜዳዎች ላይ ባለመገኘት በተደጋጋሚ ጊዜ የፎርፌ ውጤት እየተሰጠበት በመሆኑ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ  ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ባደረገው ስብስባ ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጪ እንዲሆንና በቀጣይ ከክለቡ ጋር ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች በፎርፌ ውጤት እንዲያገኙ ወስኗል። በዚሁ መሰረት መከላከያ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝቷል። በሌላ በኩል ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከድሬዳዋ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ምክንያት ራሱን ከውድድር ውጭ ማድረጉን ተከትሎ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝቷል። ድሬዳዋ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ በሊጉ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ብሏል። በ17ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር ፌደራል ፖሊስ እና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በዚህ ሳምንት ጨዋታ ያላደረጉ አራፊ ክለቦች ናቸው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ30 ነጥብ ሲመራ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ26፣ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ22 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በቀጣዩ ሳምንት የ18ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል። በሌላ በኩል በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ባህርዳር ላይ በተደረገ ተስተካካይ ጨዋታ መከላከያ ጣና ባህርዳርን በአራት የጨዋታ መደብ 3 ለ 1  አሸንፏል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በስምንተኛው ሳምንት መርሃ ግብር መካሄድ የነበረበት ቢሆንም ጣና ባህርዳር በፋይናንስ ችግር መከላከያ በተጫዋቾች ጉዳት ጨዋታው ይራዘምልን በማለት ለኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ጨዋታው ሁለት ጊዜ መራዘሙ የሚታወስ ነው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ34 ነጥብ ሲመራ፣መዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲ በ32፣ ሙገር ሲሚንቶ በ27 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 9 ቀን 2011 ዓ.ም በሚደረጉ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል። ሮቤ ላይ መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ ከወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉን አሸናፊ የሚለይ ይሆናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም