ለሰላማዊ ትግልና ለዴሞክራሲ መጎልበት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል....ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላማዊ ትግልና ለዴሞክራሲ መጎልበት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል....ምሁራን
ሰኔ 2/2011በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ኦዲፒ/ እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ መካከል ሰላማዊ ትግል እንጂ የትጥቅ ትግል ሊኖር እንደማይገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቱና የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። የመቱ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳሉት ቀደም ሲል በሀገሪቱ ለረጅም ዓመታት በተካሄደው የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ከማንም በላይ የተጎዳው ህብረተሰቡ በመሆኑ መንግስት በአሁኑ ወቅት ግጭት እንዳይነሳ ሳይሰላች በትዕግስት መወያየትና ችግሮችን የመፍታት ባህል ሊከተል ይገባል:: ኦነግና መንግስትን ለማስታረቅ የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴም የእርቅ ሥራ አድካሚ እና አሰልቺ መሆኑን ተረድቶ ያኮረፉ አካላትን ወደ መግባባት እንዲመጡ ሙሉ አቅሙን አሟጦ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባም ነው የገለጹት። ሌላኛው የህግ መምህር አቶ ዳኜ ጀምበሬ በበኩላቸው የእርቀሰላም ውሳኔውን አልቀበልም ያሉት የኦነግ ታጣቂዎች በአብዛኛው በህብረተሰቡ መካከል እንደሚገኙ ጠቁመው፣ በዚህ ሁኔታ የኃይል እርምጃን መውሰድ ከጥቅም ጉዳቱ እንደሚያመዝን አስታውቀዋል:: የኦነግ አመራር ድርጅቱ ከእዚህ በኋላ የታጠቀ ኃይል እንደሌለው መግለጹ በሀገሪቱ መተማመን ያለበት ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል። በተመሳሳይ ዜና በኦዲፒና በኦነግ መካከል የተደረሰው ስምምነት ቀደም ብለው ከተደረጉ ስምምነቶች የተለየ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ አንዳንድ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የተደረሰው ስምምነት ጥሩ ቢሆንም ሌሎች አካላትንም ባለማካተቱ ከዚህ ቀደም ከተደረገው የተለየ ነው ብለው እንደማያስቡ አመልክተዋል። “ብዙ ጊዜ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውይይት የሚያደርጉት አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ብቻ ናቸው፤ መንግስት በዚህ በኩል ቁርጠኝነቱ የላላ ነው” ብለዋል።