ባለስልጣኑ ፍትሃዊ የመንገድ ስርጭትን በተመለከተ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ግልጽነት ሊፈጥር ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ ፍትሃዊ የመንገድ ስርጭትን በተመለከተ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ግልጽነት ሊፈጥር ይገባል ተባለ
አዲስ ሰኔ 1/2011 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የክልሎችን ፍትሃዊ የመንገድ ስርጭት አስመልክቶ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ግልጽነት እንዲፈጥር የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ደጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋ ሚ ኮሚቴ አሳሳበ። ምክር ቤቱ ዛሬ በጀመረው መደበኛ ስብሰባው የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ቋሚ ኮሚቴ የ2011 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። የቋሚ ኮሚቴው ጸሀፊ አቶ ኃይሉ ኡፋ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የፌዴራል መሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊነትን በተመለከተ በምክር ቤቱ የተቀመጡ የማስተካከያ አቅጣጫዎች ላይ ክትትል ተደርጓል። በዚሁ መሰረት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ባለፉት 20 ዓመታት በፌዴራል ደረጃ የተሰሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችና አሁን በተጨባጭ ያለው ሁኔታ፣ከመንገዶች ደረጃ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ክፍተት ለማጥበብ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንዲሁም የፌዴራል መንገድ ቀጣይ አካሄድን በተመለከተ የመንግስት ውሳኔና አቅጣጫ የሚሹ ጉዳዮችን ለይቶ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት አድርጓል። ባለፉት ዓመታት በባለስልጣኑ ተግባራዊ በተደረጉ የልማት ፕሮግራሞች መንገዶች ሲገነቡ ታሳቢ የሚደረገው በዋናነት የመንገዶች ባህሪና አጠቃላይ ፋይዳ እንጂ ለየክልሉ ሊዳረስ የሚገባው የመንገድ አውታር መጠንና አይነት በኮታ መልክ በመቀመር አስቀድሞ በመወሰን እንዳልነበር ሪፖርቱ አመላክቷል ብለዋል ጸኃፊው። መንገዶች ከተገነቡ በኋላም በክልሎች መካከል ያለውን የስርጭት ሁኔታ የህዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት ታሳቢ በማድረግና በትግበራ ወቅት የጎላ ያለመመጣጠን መኖር አለመኖሩን በክትትል ይደረግ እንደነበር ተገልጿል። ይህ ክትትል ግን የመንገድ ግንባታው የስርጭት ፍትሃዊነት በማያወላዳ መልኩ ማሳየት የሚችል፣ አስቀድሞ በተወሰኑና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መግባባት በተደረሰባቸውና ከማንኛውም የመንገድ ግንባታ በፊት ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ በሚደረጉ መስፈርቶች አመሰረት አለመሆኑ ታይቷል። በተጨማሪም ባለስልጣኑ በህገ መንግስቱና በአዋጅ ከተሰጠው ሀላፊነት ውጪ በክልል ደረጃ ሊሰሩ የሚገባቸውን መንገዶች መገንባቱ ባለፉት አመታት ከተስተዋሉ ክፍተቶች መካከል ተጠቅሷል። ከተከናወኑ የመንገድ ልማት ፕሮግራሞች መካከልም የተሰሩ መንገዶች ቅደም ተከተልና የተሰሩበት ደረጃ በተመለከተ በተጨባጭ የሚስተዋሉ ክፍተቶችም እንዲሁም። የመንገዶችን ደረጃ ለመወሰን ጥናት በሚያካሂዱ አማካሪዎች ሆን ተብሎ ወይም በስህተት በሚደረግ መረጃን ለዋውጦ የመጠቀም ተግባርና አልፎ አልፎ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የአመራር አካላት ጣልቃ ገብነትና ጫና የመንገዶች ደረጃ ሲወሰን ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተጽዕኖ መኖሩ ለክፍተቶች በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። በአጠቃላይ በአገሪቱ ለመንገዶች ደረጃ ልዩነትና ያለመመጣጠን በቂና አሳማኝ ምክንያት መስጠት እንዳልተቻለም ሪፖርቱ አመላክቷል። ባለስልጣኑ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማጥበብ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ጸኃፊ ይህ መልካም ጅማሬ መሆኑን አክለዋል። ለአብነትም በግንባታ ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል የአራቱ ደረጃ እንዲሻሻል ተወስኖ ተግባራዊ መደረጉና የመንገዶችን የአገልግሎት ደረጃ ለመወሰንና የክልሎችን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ አማካሪዎችን ግዢ ፈጽሞ ጥናት መጀመሩ ተጠቅሷል። በቀጣይም ባለስልጣኑ የሚያከናውናቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች የሚመረጡባቸውን መስፈርቶች መወሰንና የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል። የተስተዋሉ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የህግ አውጭውና ህግ አስፈጻሚውን አቅጣጫና ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ የፌዴራልና የክልሎችን ሚና መወሰንና ከበጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተከታትሎ ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅበታልም ተብሏል። ከግልጽነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስቀረትም በፌዴራል ደረጃ የሚሰሩ መንገዶች በማስተር ፕላን መልክ ተጠንተው የሚመለከታቸው አካላት ከጅምሩ ተሳትፈውና አስቀድመው አውቀውት እንዲተገብሩት ማድረግ እንደሚያሻም ተጠቁሟል። ባለስልጣኑ ክፍተት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት ወቅታዊ ምላሽ መስጠትና ለህብረተሰቡ ጥያቄዎችና ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጥም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።