ፍትሃዊ የመሰረተልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የማካካሻ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ፍትሃዊ የመሰረተልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የማካካሻ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል
ሰኔ 1/2011 ፍትሃዊ ያልነበረውን የመሰረተልማት ተደራሽነት ችግር ለመፍታት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የማካካሻ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ተነገረ። ይህ የተነገረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ 5ኛ የፓርላማ ዘመን አራተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ ነው። የምክር ቤቱ የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ቋሚ ኮሚቴ የተወያየበትን የ2011 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርት በስድስት ተቃውሞና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል። የቋሚ ኮሚቴው ፀሀፊ አቶ ኃይሉ ኡፋ እንደገለጹት ምክር ቤቱ ቀደም ሲል በሰጠው የማስተካከያ አቅጣጫ መሰረት በአራት የመሰረተ ልማት አውታሮች አፈፃፀም ላይ ክትትል አድርጓል። በክትትሉ መሰረትም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ኢትዮ-ቴሌኮም ክልላዊ ስርጭቶችን የሚፈፅሙበትን መስፈርት፣ የአገልግሎት ሽፋናቸውንና ቀጣይ ስራዎቻቸውን የተመለከተ ሰነድ ለምክር ቤቱ ልከዋል። መስፈርቶቹ በተቋማቱ ተዘጋጅተው ቢቀርቡም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት መፍጠር እንደሚገባቸው ገልፀዋል። የመንገድና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሚሰሩ ተቋማትም መስፈርቶቻቸውን የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጁ መሆኑን መግለፀቸውን አብራርተዋል። ምክር ቤቱ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ኤርፖርቶች ድርጅት ባደረገው የዳሰሳ ጥናትም ተቋማቱ የመሰረተ ልማት አውታሮች ሲዘረጉ የሚከተሏቸው የየራሳቸው አሰራሮች እንዳሏቸው መገንዘቡን አውስተዋል። የአብዛኞቹ ተቋማት መስፈርቶች ግልፅነት የጎደላቸውና የስርጭት ፍትሃዊነትን የማመላከት ውስንነት የሚታይባቸው መሆናቸውን በማመላከት። እነዚህ ተቋማት በቀጣይ ግልፅ የመሰረተ ልማት ስርጭት መስፈርቶችን በማዘጋጀትና ግብዓት በመቀበል ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚያደርጉት ስምምነት መሰረት ስራዎችን መከወን እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል። ምክር ቤቱ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ላይ በተለይም ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ሰፊ ክፍተት መኖሩን አንስቷል። ሆኖም የምክር ቤቱ አባላት ፍትሀዊ ተጠቃሚነት መኖርና አለመኖሩ ላይ ሰፊ ክርክር አካሂደዋል። ክርክሩ ስርጭቱ ላይ የፍትሀዊነት ችግር ካለ በገለልተኛ አካል በተደረገ ጥናትና በተለዩ መስፈርቶች ተመስርቶ ሊሆን ይገባል እና ፍትሀዊነት አለመኖሩ በቋሚ ኮሚቴው ግምገማና በኀብረተሰቡ አስተያየት መረጋገጥ ይቻላል በሚሉ ሁለት ሃሳቦች ነው የተካሄደው። በቀጣይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራዎችን በመስፈርት በመስራት ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና የማካካሻ ስራዎችን ማከናወን እንዳለባቸውም ተጠቁሟል። የምክር ቤቱ አባላት በሪፖርቱ መረጃ ለመስጠት ተባባሪ ያልነበሩ ተቋማት እንደነበሩ በመመላከቱ በእነዚህ ተቋማት ላይ የተጠያቂነት አሰራር ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል። የመሰረተ ልማት አቅራቢ ድርጅቶችም የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችን እንደ ግብዓት እንደሚወስዷቸው ገልፀው ስራዎቹ በፌዴራል ደረጃ ብቻ የማይሰሩና በክልልም ቅንጅትን የሚሹ መሆናቸውን ተናግረዋል። በሪፖርቱ በቋሚ ኮሚቴው የታቀዱ፣ የተከናወኑና ያልተከናወኑ ቀሪ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ተመላክተዋል። ምክር ቤቱ እስከ መጪው ሰኞ በሚቆየው መደበኛ ስብሰባው የድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል የሚመራበት ስርዓት ረቂቅ አዋጅ፣ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ጊዜ ስለማራዘም የቀረበ የውሳኔ ሀሳብና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።