ለአገር አቀፍ ፈተናዎች አስፋለጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
ለአገር አቀፍ ፈተናዎች አስፋለጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል
ግንቦት 30/2011 በመላው ኢትዮጵያ በመጪው ሳምንት ለሚካሄዱት ብሔራዊ ፈተናዎች አስፋለጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ዘንድሮ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የ10ኛ ክፍል፤ ከ300 ሺህ የሚልቁ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሚኒስቴሩ ከአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ጋር በመሆን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ እንደገለጹት ለዘንድሮ አገር አቀፍ ፈተናዎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተገቢው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል። ተፈታኝ ተማሪዎች በፈተና ወቅት ችግር ሲያጋጥማቸው ጥቆማ የሚያደርጉበት አሰራር ተዘርግቷል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ ተማሪዎች በፈተና ላይ ሊገጥማቸው የሚችለውን መረበሽ ለመከላከል ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአህምሮ ጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በተለያዩ ቋንቋዎች አስተማሪ የሆኑ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የሚያስችል ዝግጅትም ተደርጓል ብለዋል። አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና ግለሰቦችን ጨምሮ መላው ህዝብ ተፈታኝ ተማሪዎች በሰዓታቸው ፈተናው ላይ በመቀመጥ ተረጋግተው መፈተን ይችሉ ዘንድ ቅድሚያ በመስጠትና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ እንዲተባበርም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህም ሌላ ህዝቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ለሚሰራጩ አሉባልታዎች ቦታ ባለመስጠት የተሳሳቱ መረጃዎች ተሰራጭተው ተፈታኞች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጠርም የበኩሉን ሚና እንዲጫወት አሳስበዋል። መንግስት ከማህበራዊ የመረጃ አውታር ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ተገቢ ያልሆኑ የሀሰት መረጃዎችን በሚያስተላልፉ ግለሰብና አካላት ላይ አካውንት መዝጋትን ጨምሮ ሌሎች ህጋዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚሰራም ገልጸዋል። ፈተናው እንደተጠናቀቀ ተፈታኞች በክረምቱ በበጎ ተግባር መሳተፍ የሚችሉበት መርሃ ገብርም መዘጋጀቱን ወይዘሮ ፅዮን አክለዋል። በዚህ የበጎ ተግባር መርሃ ግብር በመላው አገሪቱ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ከሶሰት መቶሺህበላይ ተማሪዎች ድጋፍ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረ እግዚአብሄር በበኩላቸው እንደገለጹት የ8ኛ፣ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል የቀን፣የግልና የማታ ተማሪዎችን ለመለየት የሚያስችል የኦላይን ምዝገባ ተደርጓል። ዘንድሮ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የ10ኛ ክፍል፤ ከ300 ሺህ የሚልቁ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህን ተማሪዎች ለመፈተን የሚያስችሉ የፈተና ጣቢያዎችና ከ82 ሺህ በላይ የሰው ኃይል ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል። ፈተናዎቹም ሳይንሳዊ በሆነ ይዘት ተዘጋጅተውና ህትመታቸው ተጠናቆ በየብስ፣ በአየርና በሄሊኮፕተር የሟጓጓዝ ስራ ከፌደራል ፖሊሲና ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ተከናውኗል። ለፈታኞችና የፈተናአስተባባሪዎች የሚሆን 220 ሚሊዮንብርበላይበጀትመመደቡንምዋናዳይሬክተሩጠቅሰዋል። የዘንድሮ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና የ10ኛ ክፍል ከሰኔ 03/201ዓ.ም እስከ ሰኔ 05/2011 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን የ12ኛ ክፍል ፈተና ደግሞ ከሰኔ 06/2011 ዓ.ም እስከ ሰኔ 11/2011ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ባለው መንገድ ይካሄዳል።