ማንነታቸው በማይታወቁ ግለሰቦች ለዝርፊያ መዳረጋቸውን በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ማንነታቸው በማይታወቁ ግለሰቦች ለዝርፊያ መዳረጋቸውን በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች ተናገሩ
ግንቦት 30/2011 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሐረማያ ወረዳ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦች ዝርፊያ እየፈጸሙብን ነው ሲሉ ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች ተናገሩ። በተሽከርካሪዎች ላይ ዝርፊያ ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል። በአገር አቋራጭ ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር የመጡት አቶ ሐፊዝ አባጎጃም እንደተናገሩት በወረዳው ደንገጎ በሚባል አካባቢ ማንነታቸው የማይታወቅ ሁለት ግለሰቦች ይጓዙበት የነበረውን ተሽከርካሪ አስቁመው በማስፈራራት ከተሳፋሪው ላይ ገንዘብ ዘርፈው ተሰውረዋል። “በአካባቢው ምንም ዓይነት የጸጥታ አካል ባለመኖሩ ለማሳወቅ ተቸግረን ወደ ሐረር ከተማ ልንጓዝ ተገደናል፤ ለችግሩ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ይስጥበት” ሲሉም ተናግረዋል። “በህገ ወጥ መንገድ ወደ አረብ አገር የምትኮበልሉ በመሆናችሁ ገንዘብ ካላመጣችሁ አታልፉም እያሉ በማስፈራራት በተደጋጋሚ በወረዳው የተለያዩ ስፍራዎች ዝርፊያ ይፈጸምብናል” ያለችው ደግሞ በንግድ ስራ የተሰማራችው ወይዘሮ ፋጡማ ተማም ናት። በአካባቢዎቹ የፖሊስ ጣቢያዎች ቢኖሩም በውስጣቸው የጸጥታ አካላት ስለሌሉ የወንጀል ድርጊቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን ተናግራለች። “በየጊዜው በተሳፋሪዎችና በአሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸመው ወንጀል ስጋት እየፈጠረ በመሆኑ መንግስት መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል” ሲሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግራል። የአገር አቋራጭ አሽከርካሪው አቶ አለኽኝ ወንድሙ በበኩሉ ከዛሬ ሶስት ወር በፊት ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ስንጓዝ ደንገጎ ቀበሌ ላይ ዘራፊዎች አስቁመው ከእያንዳንዱ ተሳፋሪ ገንዘብ ወስደው መሰወራቸውን አስታውሷል። “በቅርቡም በተመሳሳይ ስፍራ ላይ የወንጀል ድርጊቱ ዳግም ተፈጽሞብናል፤ ለድሬዳዋ አስተባባሪያችን ጉዳዩን ብናመለክትም መፍትሄ ልናገኝ ስላልቻልን መንግስት ችግሩን በፍጥነት ሊፈታልን ይገባል” ብሏል ። የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንግስት ኮሚኒንኬሽን ዲቪዝን ኃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፋ የወንጀል “ድርጊቱ በአገር አቋራጭ ተሽከርካሪ ላይ ብቻ ሳይሆን በከባድ የጭነት መኪና ላይም መፈጸሙን ለፖሊስ መረጃ ደርሷል” ብለዋል። “ፖሊስ ባደረገው እንቅስቃሴ ዝርፊያ ሲፈጽሙ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 30 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳቸው በፍርድ ቤት እየታየ” ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል። በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የድሬዳዋ አስተዳደር፣ የሐረማያና የቀርሳ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል። እንደ ኮማንደር ስዩም ገለጻ ተጠርጣሪዎቹ የዝርፊያ ወንጀሉን የፈጸሙት ደንገጎ፣ ሐረማያና ቀርሳ ወረዳዎች በሚገኙ አሳቻ ቦታዎች ላይ ነው። “በአሁኑ ወቅት በቦታው ላይ ከመደበኛ ፖሊስ በተጨማሪ ልዩ ኃይል የፖሊስ አባላት ተሰማርተው የክትትል ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛል” ብለዋል። በዞኑ አሽከርካሪዎችን በማስቆም ሆነ እየተጓዙ የሚከናወኑ የወንጀል ደርጊቶችን ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም የዞኑ ፖሊስ ከአጎራባች ክልል የጸጥታ አካል ጋር በመተባበር የተቀናጀ ስራ እንደሚያከናውንም ኮማንደር ስዩም ጨምረው ተናግረዋል።