ቀጥታ፡

ዩኒቨርስቲው 11 የጥናትና ምርምር የጽሁፍ ሥራዎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ የአገሪቷን ቋንቋና ባህል የሚያጎለብቱ 11 የጥናትና ምርምር የጽሁፍ ሥራዎችን አስመረቀ። ከተመረቁት መጻሕፍት መካከል በ16 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ባሕሬይ የተጻፉት "መዝሙረ ክርስቶስ" እና "መጽሐፈ ባህርይ" ይገኙበታል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንደገለጹት ዩንቨርሲቲው በአገር ውስጥ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች ለምርቃት ያበቃቸው መጽሐፎች "አገር በቀል እውቀቶችን ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል"። የተመረቁት መጽሐፎች ብዙ ገንዘብ፣ እውቀት፣ ጊዜና ጉልበት ፈሶባቸው የተገኙ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። የታተሙት የምርምር ውጤቶች ለቋንቋዎቹና ባህሎቹ ባለቤት ለሆኑ ማሕበረሰብ፣ በተለያዩ ደረጃ ላይ ላሉ አስፈጻሚ አካላትና በምርምር ሥራ ላይ ለሚሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በአንድ ጊዜ 11 መጽሐፎች እንዲታተሙ ላደረገው ጥረትም ምስጋና ይገባዋል ብለዋል። ምቹ ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ በመዘዋወር መረጃዎችን በማሰባሰብ የምርምር ሥራዎቹን ለውጤት ላበቁ የአካዳሚው ተመራማሪዎችም ምስጋናቸውን አቅርበው፤ በቀጣይ ሚኒስቴሩ የተሻሉና ጥራት ያላቸው የምርምር ሥራዎች በብዛት እንዲወጡ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም ሚኒስትሯ ቃል ገብተዋል። የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው በአገሪቷ የሚገኙ ቋንቋዎችና ባህሎች እንዲጠበቁና ለትውልድ እንዲተላለፉ፤ እንደዚሁም ህፃናት በቋንቋቸው እንዲማሩና ቋንቋና ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ የምሁራን እገዛና ድጋፍ  አስፈላጊ ነው። ብዙ ገንዘብ፣ እውቀት፣ ጊዜና ጉልበት ፈሶባቸው ለምርቃት የበቁት የምርምር ውጤቶች እምቅ ባህሎችና ቋንቋዎች ውስጥ ያሉ አገር በቀል እውቀቶች እንዲስፋፉና እንዲተዋወቁ ከፍተኛ አስተዋጾኦ ይኖራቸዋል ብለዋል። በተጨማሪም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተግባር ክህሎት እንዲያድግና እንዲጎለብት፣ የመማርና ማስተማር ሂደት እንዲቀናጅም ያድርጋል። በመሆኑም በዩንቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚን ጨምሮ 10 ተቋማት ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸውን ጥናትና ምርምር አድርገው እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል ሲሉም አክለዋል። ከተመረቁት መጻሕፍት መካከል መዝሙረ ክርስቶስ፣ መጽሐፈ ባህርይ፣ የአርሲ ኦሮሞ ባህል፣ ኦሮምኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት፣ የአዊኛና አማርኛ ቋንቋዎች ንጽጽራዊ ትንተናና አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ለመማርና ለማስተማር የሚያስችል፣ ማሌ፣ ሃሮ፣ ሙሲታቻ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አማርኛ-እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ይገኙበል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም