ቀጥታ፡

በቡራዩ ከተማ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ከወንጀል ፈጻሚዎቹ ጋር ተያዘ

ግንቦት 30/ 2011በቡራዩ ከተማ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ በከተማው የጸጥታ ኃይል እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በተካሄደ ዘመቻ ለወንጀል ድርጊት ሊውል የነበረ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የከተማው ጸጥታ ዘርፍ አስታወቀ። የቡራዩ ከተማ የአስተዳደር የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ኮሚሽነር ሰለሞን ታደሠ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ለወንጀል ድርጊት ሊውል የነበረ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር የዋለው ዛሬ ንጋት ላይ ኅብረተሰቡ፣ የከተማው ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የከተማው የጸጥታ ዘርፍ በጋራ በመቀናጀት ባከሄዱት ዘመቻ ነው። በዘመቻውም 148 የተለያዩ ሽጎጦች እና ሶስት ሺህ 844 ጥይቶች ከሁለት ግለሰቦች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኮምሽነሩ አስረድተዋል። የከተማዋን ጸጥታ ለማስጠበቅ ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረቡት ኮምሽነር ሰለሞን፤ የቡራዩ ከተማ የጸጥታው ዘርፍ የከተማዋን ሠላም ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የሚያካሂደውን ዘመቻ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በትናንትናው ዕለት በቡራዩ ከተማ በተካሄደው ተመሳሳይ ዘመቻ አባ ቶርቤ (ባለ ሳምንት) በመባል የሚታወቅና የኅብረተሰቡን ሰላም የሚነሳ ቡድን አራት አባላት ከሁለት ማዳበሪያ የመከላከያ ሠራዊት አልባሳትና ሌሎች ቁሶች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም