ለአገር አቀፍ ፈተናዎች መዘጋጀታቸውን የጋምቤላ ክልል ተማሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለአገር አቀፍ ፈተናዎች መዘጋጀታቸውን የጋምቤላ ክልል ተማሪዎች ገለጹ
ጋምቤላ ግንቦት 30/ 2011 በጋምቤላ ክልል ከመጪው ሣምንት ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው ፈተና ዝግጅት ማድረጋቸውን አንዳንድ ተፈታኞች ገለጹ፡፡ በጋምቤላ ክልል ከመጪው ሣምንት ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጡት ፈተናዎች ዝግጅት ማድረጋቸውን አንዳንድ ተፈታኞች ገለጹ፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለመስጠት ዝግጅት አድርጌያለሁ ብሏል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አንዳንድ የጋምቤላ ከተማና የአቦቦ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደገለጹት ከሰኔ 3 ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱት የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች ዝግጅት አድርገዋል፡፡ እንደ ተማሪዎቹ ገለጻ በክፍል ውስጥ ከተማሩት በተጨማሪ ከጓደኞች ጋር በመሆን የማጣቀሻ መጻህፍትን በማንበብና ያለፉ ፈተናዎችን ሰርተዋል፡፡ በተለይም የፈተና ጊዜው መራዘም ዝግጅት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል። ከተፈታኝ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ኡሞድ ኡጁሉ በሰጠው አስተያየት ለአገር አቀፉ ፈተና ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ የተማርኩትን በመከለስ ራሴን ለፈተናው አዘጋጅቼያለሁ ብሏል፡፡ በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት ፈተናዎች ከጓደኞቹ ጋር በመሥራትና ሌሎች ማጣቀሻ መጻህፍትን በማንበብ የፈተናውን ቀን እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ለዚህም የፈተናው ጊዜ መራዘም ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት ተናግሯል፡፡ ተማሪ ሙሉ ደጉ በበኩሏ በክፍል ከተማረችው በተጨማሪ የተለያዩ አጋዥ መጻህፍትን ማንበቧን ትገልጻለች፡፡ በተለይም ከኩረጃ ጋር ተያይዞ ማነኛውም ተማሪ በተማረውና በተዘጋጀው ልክ ፈተናውን መውሰድ እንጂ ሌላውን ተማሪ መረበሽ እንደሌለበትም ተናግራለች፡፡ ለፈተና ባነበበው ልክ መዘጋጀቱን በመጠቆም ኩረጃን እንደሚጠየፍ የተናገረው ደግሞ ሌላው ተማሪ ቲያም ዴንግ ነው፡፡ በተለይም ኩረጃ ከተማሪው አልፎ ለአገርም ሸክም በመሆኑ ሁላችንም በምንችለው መልኩ ኩረጃ እንዳይኖር መከላከል አለብን ብሏል፡፡ በጋምቤላ መምህራን ኮሌጅ የሥነ ልቡና መምህር ኡማን ሌሮ እንዳሉት ተማሪዎች ወደ ፈተና በሚገቡበት ጊዜ ውጤታማ ለመሆን ከፍርሃት በመውጣት ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ከመጨናነቅ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ለመፍታት ራሳቸውን በመረጋጋትና ፈተናው ከተማሩት ውጭ እንዳልመጣ ራሳቸውን በማሳመን ወደ ፈተና መግባት አለባቸው ብለዋል፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ የማሎ በክልሉ የሚሰጡ ፈተናዎችን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ይህንም ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው ኮማንድ ፖስት በማቋቋም እየተሰራ መሆኑንና የፈተና ወረቀቶችም ወደ መፈተኛ ጣቢያዎች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚጓጓዝ አስታውቀዋል፡፡ ፈተናውን ሰላማዊና ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን ለስኬታማነት ሁሉም በጋራ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ የጋምቤላ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊጋ ኡኬሎ እንዳሉት አስተዳደሩ ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለመስጠት የቁሳቁስና የሰው ኃይል ምደባ ተደርጓል፡፡ የአቦቦ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኡቶው ኡጁሉ በበኩላቸው ለአገር አቀፉ ፈተና የሚያደርጉትን ዝግጅት በማጠናቀቅ የፈተናውን ቀን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል በዚህ የትምህርት ዘመን ወደ 17 ሺህ የሚጠጉ የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናዎቹን እንደሚወስዱ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ለዚህም 52 የመፈተኛ ጣቢያዎችና 556 የሰው ኃይል ተዘጋጅተዋል፡፡