ለወራሪው ፍቱን መድሃኒት

38

ገብረህይወት ካህሳይ ከኢዜአ

ወራሪውን በቁጥጥር ስራ ማዋል ተችሏል የሚል የምስራች ያበሰረን የወረር ግብርና ምርምር ማእከል ነው ። የምስራቹ ለሁላችን ቢሆንም የአፋሮቹን ያክል ያስፈነደቀው ግን የለም ። ምክንያቱም የእነሱን ያክል የተወረረ አልነበረምና ።

ወራሪው አረም በሳይንሳዊ ስሙ ፕሮሶፒስ ጂሊፍሎራ ይባላል ። በተለያዩ የአገሪቷ ክፍል ወያኔ ዛፍ ብለው የሚጠሩትም በርካቶች ናቸው ። ወራሪው አረም ወደ አገራችን የገባው በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል ።

የወያኔ ዛፍ የሚል ስያሜ የተሰጠው ደግሞ ኢህአዴግ አገረቷ በተቆጣጠረበት ወቅት በእጅጉ ተስፋፍቶ በመታየቱ እንደሆነ ይነገራል ።

ፕሮሶፒስ ጂሊፍሎራ በአጋጣሚ አልነበረም የገባው ።አመጣጡ ሆነ ተብሎ በረሃማነት ለመከላከልና የእርሻ ማሳዎችን ከአባሯና ከአውሬ ለመጠበቅ እንደ አጥር ያገለግላል ተብሎ ነበር ።

በተግባር የታየው ግን የተገላቢጦሽ ነው ። ሰፊ የተፈጥሮ ግጦሽ መሬቶችን በመውረርና ብዝሃ ህይወትን በማጥፋት አርብቶ አደሩን በቀላሉ ለድርቅ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል ። እሾሁም ሆነ ፍሬው ለቤት እንስሳት ጠንቅ ነው ። ለሞትና ለአካል ጉዳት ያጋልጣቸዋል ።

ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ጊዜ በአገራችን 35 አዲስ ወራሪ መጤ ዝሪያዎች ተመዝግበው ይገኛሉ ። በሚያስከትሉት ተፅእኖ መጠን ክትትል ፣ ቁጥጥርና የማስወገድ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው አራቱ ዋና ዋና መጤ ወራሪ አረሞች ግን ፕሮሶፒስ ፣ፈረምሲሳ ፣ እምቦጭና የወፍ ቆሎ ናቸው ።

ፕሮሶፒስ ጂሊፍሎራ በአፋር ክልል ብቻ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር የተፈጥሮ ግጦሽ መሬት በመውረር የመኖ እጥረት አስከትሏል ። በሶማሊ ክልል ፣ በድሬዳዋና በአርባ ምንጭ አካባቢም ቢሆን በአስደንጋጭ ሁኔታ መስፋፋት ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል ።

መንግስት አሳሳቢነቱን በመገንዘብ ስርጭቱን ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ መክሮበታል ። በሰው ሀይል ነቅሎ በማቃጠል ለማስወገድም ተደጋጋሚ ጥረት ተደርጓል ። ውጤቱ ግን ” ከእጅ አይሻል ዶማ ” ዓይነት ሆኖ ዘልቆ ነበር ።

በሰው ጉልበት ተነቅሎ ስሩ በእሳት የተቃጠለ አንድ የወራሪው አረም ዛፍ አንድ ሺህ ሆኖ እየበቀለ አስቸግሮ መቆየቱን የወረር ግብርና ምርምር ማእከል ተወካይ አቶ አሸናፊ ወርቁ ይናገራሉ ።

በአሚባራ ወረዳ የመልካ ወረር ነዋሪ አርብቶ አደር መሀመድ ሁሴን አንቱታ እንደሚሉት ከሆነ መጤ ወራሪው አረም ወደ አካባቢያቸው ከገባ ወዲህ የግጦች ሳርና ለመኖነት የሚያገለግሉ እፅዋቶችን በሙሉ አጥፍቶአቸዋል ።

ከዚህም ባሻገር የአረሙ እሾህ የቤት እንስሳትን በመውጋት ዓይናቸው እንዲጠፋ ፣ እግራቸው እንዲያነክስና መንጋጋቸው እንዲጣመም ከማድረግ ባሻገር ለሞትም ጭምር ይዳርጋቸዋል ።

ሴት አርብቶ አደር ፋጡማ ዓሊ በበኩላቸው መጤው ወራሪ አረም ሲነሳ ባደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት እንባ ይተናነቃቸዋል ። ” በቅርቡ 15 በግና ፍየሎች ገድሎብኛል ። ቤተሰቦቼም በተደጋጋሚ ጊዜ በአረሙ ምክንያት ግመሎቻቸውን አጥተዋል ” ይላሉ ።

የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ፅህፈት ቤት ዋና ሃላፊ አቶ ሽፈራው መንግስቴ በአረሙ በእጅጉ ከተማረሩ ሰዎች መካከል ይካተታሉ ። በፓርኩ ክልል በፍጥነት የተዛመተው መጤ ወራሪ አረም ለዱር እንስሳቱ ምግብ የሚሆኑ ሳሮችና ቅጠላቅጠሎችን በማጥፋት ችግር እየፈጠረ ነው ይላሉ ።

አሁን ግን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወረር ግብርና ምርምር ማእከል የምስራች ! ይለናል ። ወራሪውን አረም በማያዳግም ሁኔታ የሚያደርቅና በዘላቂነት የሚያስወግድ መፍትሔ አግኝቻለሁ ይላል ።

የመፍትሔው ቁልፍ መሳሪያ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ የተገኙ ሁለት የኬሚካል ዓይነቶች ናቸው ። ኬሚካሎቹ ካቪ ከተባለ ዓለም አቀፍ የምርምር ማእከል የተገኙ ናቸው ። የወረር ግብርና ምርምር ማእከል የኬሚካሎቹን ፍቱንነት ማረጋገጡን የማእከሉ ተወካይ ይናገራሉ ።

አንደኛው የኬሚካል ዓይነት የወራሪው አረም ስር እስከ 15 ሳንቲ ሜትር ከፍታ ድረስ በመርጨት፣ ሁለተኛው ኬሚካል ደግሞ አረሙን ከታች ቆርጦ በመቀባት በቀላሉ ማስወገድ ተችሏል ።

ኬሚካሎቹ አረሙን በመጀመሪያው አምስት ቀናት ብጫ መልክ እንዲይዝና በ15 ቀናት ውስጥ በማድረቅ እንዲጠፋ የማድረግ አቅም አላቸው ።

በኬሚካሎቹ እንዲወገድ የተደረገው አረም መልሶ ያቆጠቁጥ እንደሆነ ለማረጋገጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት የዝናብ ወቅቶችን መጠበቅ አስፈልጎ ነበር ። አቶ አሸናፊ ውጤቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ” አረሙ ተመልሶ ህይወት የመዝራት አቅም አላገኘም ” ብለዋል ።

የኬሚካሎቹ ፍቱንነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከጊዜና ከገንዘብ አንፃርም አዋጪነታቸው መስክሮላቸዋል ። በትንሽ ገንዘብና በጥቂት የሰው ሃይል ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚቻል በተግባር ተረጋግጧል ።

አረሙን በሰው ጉልበት ከአንድ ሔክታር መሬት ለማስወገድ በአንድ ቀን ከ30 እስከ 40 የሚደርስ የሰው ሃይል ማሰማራት ይጠይቃል ። በኬሚካል ግን አንድ ሰው በቀን እስከ 6 ሔክታር መሬት ድረስ ከአረም ነፃ አድርጎ መዋል ይችላል ባይ ናቸው ።

ከወጪ አንፃርም በሰው ጉልበት ከአንድ ሔክታር መሬት አረሙን ነቅሎ ለማስወገድ ከ9 ሺህ እስከ 13 ሺህ ብር ድረስ ይጠይቃል ። በኬሚካል ግን አረሙን ከአምስት ሔክታር መሬት ለማስወገድ ወጪው በ12 የአሜሪካን ዶላር ብቻ የሚገዛ አንዱን ሊትር በቂ ነው ። ይህም ገፋ ቢል ከ400 ብር የሚበልጥ አይደለም ።

በመጤ ወራሪ አረሙ በእጅጉ ተጎድተው የቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አሁን በተገኘው መፍትሔ በመደሰት ኬሚካሎቹን በብዛት እንዲቀርብላቸው ይፈልጋሉ ። ለምርምር ስራ የገባ ብቻ እንጂ በገበያ እንደ ልብ አለመገኘቱ ደግሞ ሌላ ስጋት ፈጥሮባቸዋል ።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ መገርሳ ስለሁኔታው ተጠይቀው ” የምርምር ስራው በስኬት ተጠናቅቋል ። የተገኘውን አንፀባራቂ ውጤት ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት በማቅረብ ኬሚካላቹ በብዛት የሚገቡበት እድል ይፈጠራል ” ብለዋል ።

”የምስራች ! ” በማለት መልካም ዜና ላበሰረን ወረር ግብርና ምርምር ማእከል ምስር ብላ የሚል አፀፌታዊ ምላሽ በመስጠት አድናቆታችንን እየገለፅን ህብረተሰቡ የምርምር ውጤቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ጠንክሮ እንዲገፋበት የአደራ መልእክታችንን እናደርሳለን - መልካም ጊዜ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም