የቤተ እስራኤላዊያን ሙዚየም በጎንደር ከተማ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቤተ እስራኤላዊያን ሙዚየም በጎንደር ከተማ ሊገነባ ነው

ግንቦት 29/2011 የኢትዮጵያንና የእስራኤልን የቀደመ ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር በጎንደር ከተማ የቤተ-እስራኤላውያን የባህል ሙዚየም ለማቋቋም መታሰቡን በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ኦር ዳንኤላ ከጎንደር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ጋር ውይይት አድርገዋል።
"የባህል ሙዚየሙ መገንባት ኢትዮጵያና እስራኤል በደም የተሳሰረ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ በባህል፤ በቅርስ ጥበቃና በቱሪዝም ዘርፍ የሚኖራቸውን ግንኙነት ያጠናክራል" ብለዋል፡፡
"ጎንደር ከተማ የበርካታ ቤተ-እስራኤላውያን መኖሪያ በመሆኑዋ የባህል ሙዚየሙ መገንባት የከተማውን ቱሪዝም እንቅስቃሴና የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ ያግዛል" ብለዋል፡፡
በእስራኤል ሀገር ከ200ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን ቤተ-እስራኤሎች እንደሚኖሩ የጠቆሙት ምክትል አምባሳደሩ፤ የባህል ሙዚየሙ መቋቋም የከተማውን የቱሪስት ፍሰት ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በጎንደር ከተማና አካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተ-እሰራኤላውያን እንደሚገኙ የገለጹት ምክትል አምባሳደሩ፤ የቤተ-እስራኤላውያኑን ቀደምት ታሪክ፤ ባህል፤ የአኗኗር ዘይቤና ማህበራዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የባህል ሙዚየሙን ለማቋቋም የሚያስችሉ ቅድመ ጥናቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመው ከተማ አስተዳደሩ ለባህል ሙዚየሙ ግንባታ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በበኩላቸው "የቤተ-እሰራኤላውያኑ ሙዚየም በከተማው መቋቋም የሁለቱን ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያጠናክራል" ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለባህል ሙዚየም ግንባታው የሚያስፈልጉ ማናቸውንም ድጋፎች ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
"የባህል ሙዚየሙ እስራኤል ሀገር የሚገኙ ቤተ-እስራኤውያን የትውልድ ሀገራቸውን እንዲጎበኙና ታሪካቸውም ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የሚያግዝ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምክትል አምባሳደሩ ለጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የእስራኤልን ባህላዊ እሴቶች የሚያንጸባርቅ ታሪካዊ መጽሐፍ በስጦታ አበርክተዋል፡፡