እስራኤል ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች…በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
እስራኤል ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች…በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር

ጎንደር ግንቦት 29/2011 በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅምን ለማጎልበት እስራኤል ድጋፉዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ገለጹ፡፡
ምክትል አምባሳደሩ ሚስተር ኦር ዳንኤላ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆፒታልን የማህጸንና ጽንስ እንዲሁም የማዋለጃ ክፍሎች ዛሬ ጎብኝተዋል።
ምክትል አምባሳደሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት እስራኤል በዘመናዊ ግብርናና በህክምናው ዘርፍ አንዲሁም በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽንና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ ኢትዮጵያን መደገፍ ትሻለች፡፡
“ኢትዮጵያ በወጣትነት እድሜ የሚገኝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አምራች ሃይል አላት” ያሉት ምክትል አምባሳደሩ “ይህ ሃይል ለእውቀትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ነው” ብለዋል፡፡
እስራኤል የኢትዮጵያን ዩኒቨርሲቲዎች በመደገፍ በኩል ባለፉት አመታት መካከለኛና ከፍተኛ ባለሙያዎችን በእሰራኤል ሀገር የትምህርት እድል በመስጠት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል፡፡
“በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም ከእስራኤል ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎችን በማስመጣት በህክምናው ዘርፍ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን እንዲያግዙ እየተደረገ ነው” ብለዋል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የነደፈውን የጤና ፖሊሲ ለማገዝም የእስራኤል የህክምና ባለሙያዎች ቡድን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉን እየደገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እስራኤል ለዩኒቨርሲቲው መምህራንና ባለሙያዎች በርካታ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል፡፡
“ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ ከሚሆኑ አጋር የውጪ ድርጅቶች ጋር የመሰረተው ግንኙነት ለእውቀትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር እያገዘው ነው” ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጸሚ ዶክተር ሲሳይ ይፍሩ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ሀኪሞች ዘመኑ የደረሰበትን የህክምና ቴክኖሎጂ እውቀት እንዲቀስሙ እስራኤል የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠና በማመቻቸት ስትደግፍ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው አመት ለሆስፒታሉ የጥርስ ህክምና ክፍል የሚያገለግል አንድ ዘመናዊ የጥርስ ህክምና መስጫ ራጅ በኤምባሲው ትብብር ከእሰራኤል መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡
“ሆስፒታሉ እንደ ሲቲ ስካን ኤም አር አይ እና አልትራ ሳውንድ የመሳሳሉ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ቢኖሩትም በጥገና ባለሙያ እጦት በቀላል ብልሽት በርካታዎቹ ቆመው ይገኛሉ” ብለዋል፡፡
በባዮ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ እስራኤል የካበተ ልምዷን በማካፈልና የስልጠና እድል ለሆስፒታሉ ባለሙያዎች በማመቸት የቴክኖጂ ድጋፍ እንድታደርግ ዶክተር ሲሳይ ጠይቀዋል፡፡
የጎንደር ዩነቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአመት ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ህሙማን አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በህክምናው ዘርፍ ለሚያሰለጥናቸው የህክምና ዶክተሮችም የተግባር ልምምድ መስጫ ተቋም ነው፡፡