መንግስት የወጣቶችን ተፈጥሯዊ የፈጠራ አቅም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እደግፋለሁ አለ

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2011 የወጣቶችን ተፈጥሯዊ የፈጠራ አቅም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መደገፍ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ። 

ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 5 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆየው ዓለም አቀፍ የአይ.ሲ.ቲ ኤክስፖና የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሳምንት ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።

በዓለም ግዙፍ ሃብትና የስራ እድል ከሚፈጥሩት ታላላቅ ኩባንያዎች ግንባር ቀደሞቹ የአይ.ሲ.ቲ ዘርፎች መሆናቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ይሄውም ከዓለማችን 10 ግዙፍ ኩባንያዎች ሰባቱ የአሜሪካዎቹ አፕል፣ ጉግል፣ ማይክሮሶፍት፣ አማዞንና ፌስቡክ እንዲሁም የቻይናዎቹ ቴንሴንትና አሊባባ የአይ.ሲ.ቲ ኩባንያዎች ናቸው።

እነዚህ ሰባቱ ኩባንያዎች እንደአውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ20184 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ሲወጣላቸው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የዓለም ህዝቦች የስራ እድል ፈጥረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያም በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ሳይንስና ቴክኖሎጂን መተግበር የግድ ነው።

ጥራት ያለው ትምህርት፣ የተሻለ የህክምና አገልግሎት፣ ኢንዱስትሪ መር ግብርና ማምጣት የሚቻለው በቴክኖሎጂ የዳበረ አሰራር ሲዘረጋ ብቻ ነው ብለዋል።

የወጣቶችን ተፈጥሯዊ የፈጠራ አቅም በቴክኖሎጂ መደገፍ መንግስት ቅድሚያ እንደሚሰጠውም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ እድገትና በዜጎች ህይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን መተግበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመሆኑም የነገ የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን አሁን በኢትዮጵያ የተጀመረውን በአግባቡ እንጠቀምበታለን ነው ያሉት።

"ትናንት የሚገባንን ባለመስራታችን ከስልጣኔ ወደኋላ ቀርተናል" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬ ደግሞ በቴክኖሎጂ ተመሳሳይ እጣ እንዳይገጥመን መስራት አለብን ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፤ የአይሲቲ መሰረተ ልማት ገና ብዙ ሊሰራበት የሚገባ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ ከ32 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በሚማሩባቸው 39 ሺህ ትምህርት ቤቶች ሁለት ሜጋ ባይት በሰከንድ ኢንተርኔት ፍጥነት ያላቸው ከ 500 እንደማይበልጡ ገልጸዋል።

ይህ የነገ አገር ተረካቢ ዜጎችን ያለ አይ.ሲ.ቲ እውቀት እያስተማርናቸው እንደሆነ መታወቅ አለበት ብለዋል።

ለዚህም በሚቀጥለው ዓመት በአንድ ሺህ ወረዳዎች አንድ ጊጋ ባይት በሰከንድ ፍጥነት ያለው የፊክስድ ብሮድ ባንድ አገልግሎት ለማዳረስ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በግብርና፣ በጤናና ሌሎች ተመሳሳይ ዘርፎችም ችግሩ እንዳለ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ አይ.ሲ.ቲ አገራዊ ፋይዳው ታይቶ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም