ቀጥታ፡

የደቡብ ክልል የሴቶች እጅ ኳስ አሸናፊ ሆነ

ግንቦት 29/2011 የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የ2011 ዓ.ም ሴቶች እጅ ኳስ አሸናፊ ሆነ።

ከግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሲካሄድ የነነበረው ሻምፒዮና  ፍጻሜውን አግኝቷል።

በሻምፒዮናው ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ከሐረሪና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 68 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እጅ ኳስ ፌዴሬሸን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሲሳይ ተረፈ አገር አቀፍ ሻምፒዮናው መጀመሩ መልካም ቢሆንም የተሳታፊዎች ቁጥር ማነስ ውድድሩን እንዳደበዘዘው ገልጸዋል።  

ስድስቱ ክልሎችና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በውድድሩ ላይ በበጀት ምክንያት አለመሳተፋቸው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን በቅስቀሳ ረገድ የሚጠበቀውን ያህል ስራ እንዳልሰራ የሚያመለክት መሆኑን ተናግረዋል።

የውድድር መርሃ ግብር አወጣጥ፣ ጨዋታዎች በተያዘለቸው ሰአት አለመጀመር እና ለሻምፒዮናው የተመረጡት ዳኞች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ መሆናቸው የዳኞች ስብጥር እንዳይኖር እንዳደረገም አመልክተዋል።

በቀጣይ የሴቶች እጅ ኳስ እንዲያድግ እና የውድድር አማራጮች እንዲሰፉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በቅርበት በመስራት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።

የሐረሪ ክልል እጅ ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ቤተልሄም ረጋሳ በበኩሏ የተሳታፊዎች ቁጥር ማነስ የሚያሳየው ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ለሴቶች እጅ ኳስ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው እንደሆነ ገልጻለች።

የሴቶች እጅ ኳስ ዳግም እንዲያንሰራራ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ እና በቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ለመጀመር እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች እንደሆነ ተናግራለች።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ በበኩላቸው የሻምፒዮናው አላማ የሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ዳግም እንዲጀመር ማድረግና በሻምፒዮናው ላይ ቅስቀሳ በማድረግ በ2012 ዓ.ም የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መጀመር እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከሁለት ወር በፊት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በጉባኤው ላይ የሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና እንዲካሄድ ማጽደቃቸውንና መስማማታቸውን አስታውሰዋል።

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለሻምፒዮናው አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረገ ገልጸው ስድስቱ ክልሎች እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በፋይናንስ ችግር አንሳተፍም ማለታቸው ፌዴሬሽኑን እጅጉን እንዳሳዘነው ገልጸዋል።

ክልሎቹ በበጀት ችግር አንሳተፍም ማለታቸው አሳማኝ ምክንያት እንዳልሆነና የክልሎች በሻምፒዮናው ላይ ለመሳተፍ ያላቸው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በቂ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የተሳታፊዎችን ቁጥር ለማሳደግ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር ውይይት እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

የሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮናው በየዓመቱ እንደሚካሄድና የ2012 ዓ.ም የሴቶች እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ባሉት ክለቦች እንደሚጀመርና በቀጣይም የሴቶች እጅ ኳስን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በሻምፒዮናው ፍጻሜ ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል የሐረሪ ክልልን 25 ለ 15 ሲያሸንፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልን 41 ለ 10 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

ውጤቱንም ተከትሎ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል በውድድሩ ሶስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ የሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና አሸናፊ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት ጨዋታዎችን የሐረሪ ክልል አንድ ጨዋታ በማሸነፍ ሁለተኛ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልሏ መሰረት አበራ ኮከብ ተጫዋች የሐረሪ ክልል እጅ ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ቤተልሄም ረጋሳ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል።

ለሻምፒዮናው አጠቃላይ አሸናፊ የደቡብ ክልል እና ለኮከብ ተጫዋች እና አሰልጣኝ እና ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡት ክልሎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት እና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለተወዳዳሪዎቹ የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል።

ለተሳታፊዎቹ ክልሎች ከሽልማቱ በተጨማሪ የእጅ ኳስ መጫወቻ ኳስ ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም