የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 55 ሺህ 80 ቶን ምርቶችን በ2 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር አገበያየ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 55 ሺህ 80 ቶን ምርቶችን በ2 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር አገበያየ
ግንቦት 29/2011 የአኩሪ አተር ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሆነና ወደ ምርት ገበያው የሚገባው የምርት መጠንም በዛው ልክ መጨመሩ ተነግሯል።
ምርትገበያው 29 ሺህ 382 ቶን ቡና፣ 14 ሺህ 583 ቶን አኩሪ አተር፣ 8 ሺህ 902 ቶን ሰሊጥና 2 ሺህ 213 ቶን ነጭ ቦሎቄ ምርቶችን በ2 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ያገበያየው በተያዘው ወር ነው፡፡
ቡና 53 በመቶና 70 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ በማስመዝገብ የወሩን የግብይት ድርሻ ይዟል፡፡
የቡና የግብይት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዜሮነጥብ 66 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በወሩ ሁሉም የቡና አይነቶች ግብይት የተከናወነሲሆን ለውጭ ገበያ የቀረበ ቡና 69 በመቶ የግብይት መጠንና 67 በመቶ የግብይት ዋጋ በመያዝ የግብይት ድርሻውን ሲሸፍን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የቀረበው ስፔሻሊቲ ቡና ተከታዩን ደረጃ ይዟል፡፡
ለውጭ ገበያ የቀረበ ያልታጠበ 19 ሺህ ቶን ቡና ለግብይት ቀርቦ በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሲገበያይ ከዚህ ውስጥ በግብይት መጠን በቅደም ተከተል የጊምቢቡና 21 በመቶ ቄለም ወለጋ 18 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡
እንዲሁም 1 ሺህ 468 ቶን ለውጭ ገበያ የቀረበ የታጠበ ቡና በ87 ነጥብ 97 ሚሊየን ብር የተገበያየ ሲሆን በግብይት መጠን የሲዳማ ቡና 37 በመቶ፣ የይርጋጨፌ 25 በመቶ፣ የምዕራብ አርሲ 12 በመቶ የግብይት ድርሻ አስመዝግበዋል::
በዚሁ ወር በ340 ሚሊየን ብር ከተገበያየው 4 ሺህ 125 ቶን የስፔሻሊቲ ቡና ውስጥ 1 ሺህ 25 ቶን ያልታጠበ ቡና በ110 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር እንዲሁም 3 ሺህ 101 ቶን የታጠበ ስፔሻሊቲ ቡና በ229 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል፡፡
በግንቦት ግብይት 8 ሺህ 902 ቶን ሰሊጥ በ563 ነጥብ 46 ሚሊየን ብር የተገበያየ ሲሆን የሁመራጎንደር ሰሊጥ 72 በመቶ የግብይት መጠንና 74 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ የግብይቱን ድርሻ ይዟል፡፡
በወሩ 14 ሺህ 583 ቶን አኩሪ አተር ለግብይት ቀርቦ በ231 ነጥብ 29 ሚሊየን ብር እንዲሁም 2 ሺህ 213 ቶን ድቡልቡል ነጭ ቦሎቄ በ4 ነጥብ 52 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል፡፡
ድርጅቱ ለኢዜአ የላከው መግለጫ 76 ሺህ ቶን አኩሪ አተር በ1 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር ማገበያየቱንም ጠቅሷል፡፡
የአኩሪ አተር ምርት በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ሲሆን ወደ ምርት ገበያው የሚገባው የምርት መጠንም በዛው ልክ ጨምሯል ነው ያለው፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቅበላ አቅሙን በማጠናከር በቡሬ፣ጎንደር፣ ፓዌ፣ ሳሪስና ነቀምት በሚገኙት መጋዘኖቹ ምርቱን እየተቀበለ ይገኛል፡