ስድስተኛዉ አገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ በሆሳዕና እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስድስተኛዉ አገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ በሆሳዕና እየተካሄደ ነው
ሆሳዕና ግንቦት 29 / 2011 ስድስተኛው አገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
ኮንፍረንሱ እየተካሄደ ያለው "ጥናትና ምርምር ለዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር!" በሚል መሪ ቃል ነው፡፡
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸደቀ ላንቦሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በኮንፍረንሱ 60 ያህል ጥናቶችና ምርምሮች ይቀርባሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከኮንፍረንሱ ጠቃሚ የልምድ ልውውጦችና ምርጥ ተሞክሮዎች እንደሚያገኝ ተስፋ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
''ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት መፍለቂያ ማዕከላት በመሆናቸው ለአገር እድገት ያላቸው ከፍተኛ ነው'' ያሉት ደግሞ ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የፖሊሲ፣ ሕግና መረጃዎች ጥናትና ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዶክተር አየለ ሄገና ናቸው፡፡
ኮንፍረንሱ የተመራማሪዎችን አቅም የሚያጎለብትና በምርምር ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችን የሚፈቱበትን አመላካች አገራዊ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ኮንፍረንስ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ተመራማሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡