ኢትዮጵያ በተቀበለችው የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ዙሪያ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እይታ

ሃብታሙ አክልሉ  /ኢዜአ/ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ሙሉ በሙሉ መቀበሏን አስመልክተው ታዋቂ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ውሳኔው በሃገራቱ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና ደህንነትን በማስከበር ረገድ በሚኖረው አንድምታ ዙሪያ ዘገባዎቻቸውን ይዘው ወጥተዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ረጅሙ የግጭት ታሪክ እንዲያበቃ የሚያስችል ዕድል ለኤርትራ መስጠቷን ያስነበበው ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ ለመዘገብ የቀደመው አልነበረም። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሚያዝያ በበአለ ሲመታቸው ላይ ያደረጉትን ንግግር በዋቢነት ያነሳው የዜና ወኪሉ ታላቅ የፖሊሲ ለውጥ ሃገሪቷ ልታካሄድ መሆኗን በጠቀሱበት ንግግራቸው ከኤርትራ ጋር የፍላጎት ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የደም ትስስር እንዳላቸው መናገራቸውን አስታውሷል። በኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ባካሄደው ስብሰባም በአልጀርሱ የተደረሰውን የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ መቀበሉን ማስታወቁን ያስነበበው ድረ ገፁ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ሙሉ በሙሉ ፊታችንን ወደ ሰላም በማዞር አመታት የፈጀውን ስቃይ ማቆም ይገባናል’”ማለታቸውንም አክሏል። በጉዳዩ ዙሪያ ከኤርትራ በኩል የተባለ ነገር እንደሌለ ያስቀመጠው የዜና ወኪሉ የኤርትራ የመረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ኢትዮጵያ ከያዘቻቸው ቦታዎች ለቃ እስካልወጣች ድረስ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ሊሻሻል እንደማይችል የሰጡትን ቃል አስታውሷል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ያለውን ውዝግብ ለመፍታት የሚያስችል እርምጃ መውሰዱን ማስታወቁን በድረ ገፅ ዘገባው ያስነበበው ደግሞ ኤ ኤፍ ፒ ነው። ባልተጠበቀ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፓርላማ ታውጆ የነበረውን የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ባነሳበት ቅፅበት ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በስራ አስፈፃሚ ስብሰባው ላይ የተባበሩት መንግስታት የድንበር ኮሚሽን ያስተላለፈውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ መቀበሉን ማስታወቁን የመረጃ ምንጩ አትቷል። የኤርትራ መንግስትም ይሄንን ጉዳይ ከግምት በማስገባት አላንዳች ቅድመ ሁኔታ ጥሪውን በመቀበል በሁለቱ ሃገራት መካከል ለረጅም ጊዜ ጠፍቶ የቆየውን ሰላም ለማምጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በማህበራዊ መገናኛ ድረ ገፁ ላይ ማሰቀመጡንም ኤ ኤፍ ፒ አስነብቧል። ከወሰን ግጭቱ በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዟቸው ለየቅል እንደነበር የዘገበው የዜና ወኪሉ ኤርትራ ከአለም ሃገራት የመገለሏ ሁኔታ እየጨመረ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ ግን በአካባቢው የነበራት ተሰሚነትን በፈጣን ኢኮኖሚዋ በማጀብ እንዲጨምር ማድረጓን አልሸሸገም። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ልማት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል በሚል ከጎረቤት ሃገር ኤርትራ ጋር የነበረውን የረጅም ጊዜ ጦርነት ስጋት ለመቅረፍ ማሰቧን በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል መግለጿን በዘገባው ይዞ የወጣው የሬውተርስ የዜና ወኪል ሃገሪቷ እኤአ በ2000 ዓ.ም በአልጀርስ የተወሰነውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንደምትቀበል ማሰታወቋንም አክሏል። የኢትዮጵያ ውሳኔ ባለፈው ሚያዝያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ የፖሊሲ ማሻሸያዎችን ለማምጣት ሃገሪቷ መወሰኗን ከተናገሩት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ዘገባው የጠቆመ ሲሆን ሃገሪቷ ከጎረቤት ሃገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነትንም እንደገና መልከ የማስያዝ አንዱ እርምጃ እንደሆነም አስቀምጧል። መሰረቱን ለንደን ያደረገው የቲንክ ታንክ ቻትሃም ሀውስ ተንታኙ አህመድ ሶሊማን ኢትዮጵያ እየወሰደችው የሚገኘው እርምጃ አዎንታዊ መሆኑን ገልፆ ውሳኔውም ለአከባቢው ሰላምና መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን መናገሩን የመረጃው ምንጭ ይዞ ወጥቷል። “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚገባው ጉዳይ ሃላፊነት ከሚሰማው መንግስት የሚጠበቀው ሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች በባቡር እንዲሁም በመንገድ መሰረተ ልማቶች በማገናኘት ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር የሃገራቱን ብሎም የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ይገባል” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መናገራቸውን ዋቢ በማድረግ ሬውተርስ አስነብቧል። ኒውስ 24 የተሰኘው የዜና ዘጋቢ በበኩሉ ኢትዮጵያ ከአስርት አመታት በፊት ከጎረቤቷ ኤርትራ ጋር ካደረጉት ጦርነት በኋላ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ መቀበሏን ዘግቦ ለሁለት አመታት ተደርጎ የነበረው የሁለቱ ሃገራት ጦርነት የአስር ሺዎችን ህይወት መቅጠፉንም አስታውሷል። ትንሿ ሃገር ኤርትራ እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ምንም ነገር አለማለቷን የዘገበው የዜና ምንጩ ከኢትዮጵያ ከተለያየችበት እኤአ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ከሌሎች የተገለለች ሃገር ሆና መቆየቷን አስነብቧል። “የሰላም ድርድር ማካሄድ የተዘጋ አጀንዳ በነበረበት በዚያ ወቅት የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ሊገልፅ የማይችል ስቃይን አሳልፈዋል። ለሁለታችንም ሲባል የነበረው ሁኔታ መለወጥ አለበት” ሲሉም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፍፁም አረጋ መናገራቸውን ኒውስ 24 አክሏል። ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ ባላንጣዋ ጋር አድርጋው የነበረውን የሰላም ድርድር ውሳኔ ተቀበለች ሲል የዘገበው ደግሞ አሶሺየትድ ፕሬስ ነው። የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስገራሚ ማሻሻዎች ተፈፃሚ እየሆኑ ባሉበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ውሳኔ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መቀበሏን ማስታወቋን ዘገባው አመልክቷል።መረጃው አያይዞም የምስራቅ አፍሪካዋ ሃገር በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ ተቋማትን በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ ግል ለማዞር ውሳኔ ላይ መድረሷን አስነብቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለኢትዮጵያ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር “ከኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለንን ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ከኤርትራ መንግስት ጋር ጉድኝታችንን የሚያጠናክር ውይይት ለማድረግ ጠንካራ ፍላጎት አለን” ማለታቸውን መረጃው ጠቁሟል። አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበራቸውን የሁለት ወራት ስኬታማ ጊዜ ያስቀጥሉት ይሆን በሚለው ዘገባው ሲ ኤን ኤን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጠቀሰው አጭር ጊዜ ውስጥ የተገበሯቸውን ጉዳዮች ዘርዝሮ አቅርቧል። በዜና ዘጋቢው ከቀረቡት ጉዳዮች ውስጥ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን የሰላም ድርድር ውሳኔ ተቀብላ ለተግባራዊነቱ ዝግጁ መሆኗን የገለፀችበትን እና ከጎረቤት ሃገር ኤርትራ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ውጥረት ለማርገብ የወሰደችው እርምጃን በዋነኝነት ያነሳል። በዚህም ኢትዮጵያ የሰላም ውሳኔውን ለኤርትራ ህግ መወሰኛ የቤት ስራ መስጠቷን ያነሳው የሲ ኤን ኤን ዘጋቢ ሃገሪቷ ይህንን ዕድል በተገቢው ካልተጠቀመች ቀጣይነት ያለው የውስጥ አለመረጋጋት ሊገጥማት እንደሚችል ፅፏል። አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃኑ በየገፆቻቸው ላይ ይዘውት የወጡት ዘገባ እንደሚያመለክተው ሁለቱ ሃገራት ለረጅም ጊዜ ከቆዩበት ውጥረት ለመውጣት የኢትዮጵያ ውሳኔ የየሃገራቱን ብሎም የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ከማስጠበቅ አንፃር አዎንታዊ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ፅፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም