ቀጥታ፡

ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ለምታካሂዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች 100 ሚሊዮን ዩሮ ብድርና ድጋፍ ለመስጠት ስምምነት ፈረመች

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2011 የፈረንሳይ መንግስት በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራት የሚውል የ100 ሚሊዮን ዩሮ የብድርና የድጋፍ ስምምነት ፈረመ። 

ስምምነቱን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንተምስና የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ተፈራርመዋል።  

ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዩሮ 85 ሚሊዮኑ የረዥም ጊዜ ብድር ሲሆን 15 ሚሊዮኑ ደግሞ ለቴክኒክ ድጋፍ እንደሆነ ተገልጿል።  

የተገኘው ብድርና ድጋፍ የግሉን ዘርፍ ለመደገፍናለኢኮኖሚማሻሻያዎች ይውላል ተብሏል።  

ለኢኮኖሚ ማነቃቂያ ስራዎች፣የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግናየግልጽነትና የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን አይነተኛ ሚና እንዳለውም ተጠቁሟል።   

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት ሁለቱ አገራት በከተማ መሰረተ ልማት፣ በኃይል፣ በባህላዊ ቅርሶችና በኢንቨስትመንት መስኮች ሰፊ ትብብር እያደረጉ ነው።   

አገሪቷ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ፣በማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች ማሻሻያዎች እያደረገች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ 'የዛሬው ድጋፍና ብድርም ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የለውጥ እርምጃዎች መደገፏን አመላካች ነው' ብለዋል።     

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከፈረንሳይለሚደረገው ያልተቋረጠ እገዛ 'ምስጋና ያቀርባል' ያሉት አቶ አህመድ የተገኘውን ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።  

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንተምስ የአገራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው፤ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፈረንሳይ ጉብኝት ማድረጋቸው የአገራቱን የጠበቀ ትስስር ያሳያል ብለዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጉብኝታቸው ወቅት ፈረንሳይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እንድትደግፍ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰው ዛሬ የተፈረመው ድጋፍና ብድር ለጥያቄው ምላሽ እንደሆነ አብራርተዋል።  

''ዛሬ የተስማማነው ድጋፍና ብድር በፍጥነት ገቢራዊ እንደሆን የሚቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን፣ በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት እናጠናክራለን'' ሲሉም ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም