ለአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሞት ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ ይቀርባሉ…ዶክተር ደብረጽዮን

91

መቀሌ ግንቦት 28/2011 በአክሱም ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ለአንድ ተማሪ ህልፈተ ምክንያት የሆኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ መጀመሩን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደዱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ በተማሪው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።

ህይወቱ ላለፈው ተማሪ ቤተሰቦችና ጓደኞች መፅናናትን የተመኙት ዶክተር ደብረጽዮን -“ድርጊቱ አስነዋሪ ነው” ብለዋል።

“ትግራይ የብሄሮችና ብሄረሰቦች መኖሪያ መሆኗን አምኖ ለመጣ ተማሪ እንዲህ አይነት ተግባር መፈፀም ሰላም ወዳዱን የክልሉን ህዝብ ባህልና ታሪክ የማይገልፅ ነው” ብለዋል።

ድርጊቱን የፈፀሙ ተማሪዎች በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር መጀመሩን አስረድተው ተጠርጣሪዎቹ ጥፋታቸውን በማጣራት የክልሉ መንግስት ወደ ህግ የሚያቀርባቸው መሆኑን ገልጸወዋል።

በመስዋእትነት የተረጋገጠው ሰላም በጥቂት ግለሰቦች አይደፈርስም ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ “ህብረተሰቡ ሰላሙን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ መነሳት ይኖርበታል” ነው ያሉት።

በክልሉ በከፍተኛ ተምህርት ተቋማት በተለይም በአክሱም ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የጠየቁት ዶክተር ደብረጽዮን የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም