የተከሰተው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሺኝ ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቋመ

114

ግንቦት 28/ 2011 በአራት ክልሎችና በአዲስ አበባ የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሺኝ ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል መቋቋሙን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሰታወቀ። 
 በተከሰተው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሺኝ እስከአሁን የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ ፡፡ 

ወረርሺኙን በአፋጣኝ ለመቆጣጠር የሚያስችል መድኃኒቶችና የህክምና ግብአቶች በሁሉም ክልሎች ወደሚገኙ የኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መጋዘኖች እንዲከማች መደረጉንም ገልጿል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በኦሮሚያ 138፣ በአማራ 198፣ በሱማሌ 33፣ በትግራይ 8 በድምሩ 377 ሰዎች  በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ተይዘዋል።

የበሽታውን መንስኤ ለማረጋገጥ በተወሰደ ናሙናም በአማራ ሁለት፣ በትግራይ ሁለት፣ በኦሮሚያ አምስት፣ በአዲስ አበባ ሦስት ሰዎች ወረርሺኙ ያስከተለው 'ቪቢሮ ኮሌራ' የተሰኘ ባክቴሪያ መያዛቸው መረጋገጡን መግለጫው አመልክቷል።

ወረርሺኙን ባለበት ለመግታት የጤና ሚኒስትር የሚመሩት ግበረ ሃይል መቋቋሙን ያመለከተው መግለጫው፤ ችግሩ በተከሰተባቸው ወረዳዎች ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን በቦታዎቹ ተሰማርቶ ለዚህ አገልግሎት ብቻ ተብሎ በተቋቋሙ ጊዚያዊ የህክምና ማዕከላት ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡ 

በቀጣይም ወረርሺኙ እንዳይስፋፋ የክልል መስተዳድሮችና ከንቲባዎች የሚመሩት ግብረ ሃይል እንዲቋቋም ይደረጋል ያለው መግለጫው፤ ወረርሺኙ እንዳይስፋፋ የሚያገዙ የጤና ባለሙያዎች በስልጠና ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ እንደ ውሃ ማከሚያ ኬሚካል፣መድኃኒት፣ ድንኳኖች እና ሌሎች ቁሳቁሶች መዘጋጀታቸውም ታውቋል።

በአጎራባች ሀገራት ማለትም ሶማሊያና ኬኒያ የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ወደ ሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ሊዛመት ስለሚችል አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ መደረጉንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡
የመገናኛ ብዙሃንም ኅብረተሰቡን ስለወረርሺኙ በማሳወቅና በማስተማር ኃላፊነቱን እንዲወጣም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በላከው መግለጫ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም