በወላይታ ሶዶ የጎልማሶች ትምህርት ተማሪዎች ከ230 ሺህ ብር በላይ ቆጠቡ - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ የጎልማሶች ትምህርት ተማሪዎች ከ230 ሺህ ብር በላይ ቆጠቡ
ሶዶ ግንቦት 28/ 2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት የሚከታተሉ ጎልማሶች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ230ሺህ ብር በላይ ቆጠቡ፡፡
አቶ ተፈራ ሮቤ በከተማው አስተዳደሩ የኮካቴ ማራ ጫሬ ቀበሌ ነዋሪና በኮካቴ ጎልማሳ ማዕከል ተማሪ ሲሆኑ በአሁኑ ሰዓት በደረጃ ሁለት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡
በጣት ከመፈረም ወጥተው መጻፍና ማንበብ መቻላቸውን የገለጹት ጎልማሳው ከትምህርት ባሻገር፤ በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ሰርቶ ማሳያዎች እንደተሳተፉ ተናግረዋል፡፡
በተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት፣በሰብል አያያዝና በተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት በወሰዱት ስልጠና ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በትንሽ ማሳ የጓሮ አትክልት በማልማትና የዛፍ ችግኞችን በማፍላት ከ12 ሺህ ብር በላይ ቆጥቤያለሁ ብለዋል፡፡
ሌለኛዋ አስተያየት ሰጪ የሉተራን መንደር ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ዋርዲሎ ትምህርቱን መከታተል ከጀመሩ ሁለት ዓመት እንደሞላቸው ገልጸው፣ ከማንበብና መጻፍ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡
ከግል ንጽህና አጠባበቅ እስከ መጸዳጃ ቤት አያያዝ የተከታተሉት ትምህርት ጤናቸውን ለመጠበቅ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
በጓሮ አትክልት አመራረት ረገድ የሚሰጣቸው ስልጠና አቅምና መሬታቸውን በመጠቀም ገቢ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ፤ ምርቶቹን ለመግዛት ያወጡት የነበረውን ወጪ እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል።
በተሻሻሉ የላም ዝርያዎች አያያዝና እርባታው በሚያገኙት የወተት ሽያጭ ልጆቻቸውን ማስተማርና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር አቅም ፈጥሮላቸዋል፡፡
እርሳቸውን ጨምሮ 49 ጎልማሶች እየተማሩበት ባለው በአንካ ማዕከል ያሉ ጎልማሶች ከሚያገኙት ገንዘብ ከ80 ሺህ ብር በላይ መቆጠባቸውን ተናግረዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ዳይሬክተር አቶ መስፍን በቀለ ማህበረሰቡ ከትምህርት፣ከግብርና፣ከጤና መሥሪያ ቤቶችና ከኦሞ ቁጠባ ተቋም ጋር በተደረገው የተቀናጀ ንቅናቄ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በደረጃ አንድና ሁለት ከ55 በላይ የመማሪያ ማዕከላት ያሉት ከ32 ሺህ 940 በላይ ተማሪዎች ከ230 ሺህ ብር በላይ መቆጠባቸውን ተናግረዋል፡፡ይህም የቁጠባ ባህልን በማሳደግ ሚና ተጫውቷል ይላሉ፡፡
በአፈጻጸም ግንባር ቀደም የሆኑ ከ500 በላይ ጎልማሶችን በሚቀጥለው ወር በማስመረቅ መደበኛ ትምህርት የሚቀጥሉበትና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሚሰማሩበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልጸዋል፡፡
የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሰለ ወልደሰንበት ጽህፈት ቤቱ
ዘርፉን ለማዘመንና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ለሰው ኃይል ልማት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።