በግጭት፣ በመፈናቀልና በድርቅ ምክንያት ትምህርታቸውን ላቋረጡ ተማሪዎች የክረምት ማካካሻ ትምህርት ሊሰጥ ነው

148

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2011 በግጭት፣ መፈናቀልና ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ትምህርታቸውን ላቋረጡ ተማሪዎች የክረምት ማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። 


የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፥ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 ያወጣው መረጃ በዓለም ላይ 624 የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምርህርት ቤቶች ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ያመለክታል።

በኢትዮጵያም በዚህ ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት፣ ድርቅና መፈናቀል በርካቶች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተሰደው ለችግር መዳረጋቸው ይታወቃል።

በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችም የአንድ መንፈቀ-ዓመት ትምህርታቸውን መከታተል ሳይችሉ ቀርተዋል።

በዚህ ምክንያት ትምህርታቸውን ላቋረጡ 300 ሺህ ተማሪዎች የክረምት ማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

በሚኒስቴሩ የትምህርት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ዎጋሶ እንደገለጹት፤ ግጭት፣ መፈናቀልና ድርቅ በተከሰተባቸው በደቡብ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ አካባቢዎች ቡድን ተዋቅሮ ጥናት ሲደረግ ቆይቷል።

300 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ያቋረጡትንም ለማካካስ ከሰኔ 2011 ዓም እስከ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓም ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ለዚህም ስድስት ሺህ ተመራቂ ተማሪዎች በእነዚህ አካባቢዎች ተሰማርተው በበጎ ፈቃድኝነት ትምህርት የሚሰጡ ይሆናሉ።

ይህን የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት በአጠቃላይ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን ከግል ትምህርት ቤቶች፣ ከአጋር አካላት፣ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ከግለሰቦች፣ ከተማሪዎችና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ባለሃብቶችን ያሳተፈ ገቢ ማሰባሰቢያ ሁለት የእራት ፕሮግራሞችን እንደሚካሄዱም አስታውቀዋል።

ለተማሪዎቹ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የትራፊክ አገልግሎት፣ የአካባቢ ጉዳዮች፣ የጤና እና ሌሎችንም ትምህርቶች እንዲያገኙ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ በድርቅ፣ በመፈናቀልና በግጭት ምክንያት 813 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም 564ቱ ተከፍተዋል።

ለ174 ሺህ ተማሪዎችም የተለያዩ የትምህርት መደገፊያ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል።ሌሎች ሙሉ ለሙሉ የወደሙና መገንባት ያልቻሉ ትምህርት ቤቶችም መኖራቸውንና ጊዜያዊ የመማሪያ ጣቢያ እንደሚገነባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም