ጄኔራል ሳሞራ የኑስ እጅግ ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት ተበረከተላቸው

138
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 ጠቅላይ ኢታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ የአገሪቷ እጅግ ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት ተበረከተላቸው። ጄኔራል ሰሞራ ይህንን ከፍተኛ የክብር ሽልማቱን ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እጅ ተቀብለዋል። የክብር ሽልማቱ የተበረከተላቸው ከተዋጊነት እስከ አዋጊነትና እስከ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታ ማዦር ሹምነት ድረስ አገራቸውን በትጋትና በታታሪነት በማገልገላቸው መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ጎን ለጎንም በመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ባስገኙት ውጤት፣ "ባሳዩት የአመራር ብቃትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ላበረከቱትም የላቀ አስተዋጽዖ ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋል" ነው ያሉት። "ሰራዊቱ ለሕዝብ የወገነና ከብረት የጠነከረ ሕገ-መንግሥታዊ እምነት እንዲኖረውም በዲስፒሊን የታነጸ እንዲሆንና በውትድርና ሳይንስ የታጠቀ እንዲሆን ጄኔራል ሳሞራ ሰርተዋል" ብለዋል። ከሠራዊት ምስረታ ጀምሮ "የሠራዊቱን አባላት በሂደት በመገንባት ዛሬ የመከላከያ ሰራዊት አሁን ለደረሰበት ደረጃም የእርሳቸው አስተዋጽዖ የጎላ በመሆኑም ምስጋና ይገባቸዋል" ብለዋል። በዚህም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 71 ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረት በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ማምሻውን በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የኒሻን ሽልማቱ ለጄኔራሉ ተበርክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በዚሁ ወቅት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አድርገው ሾመዋል። ቀደም ሲል ወታደራዊ ማዕረጋቸው ተነጥቆባቸው የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ እና ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌም ማእረጋቸው ተመልሶላቸው ከሙሉ የጡረታ ጥቅማጥቅም ጋር እንዲሰናበቱ ወስነዋል። ጄኔራል ሳሞራ ከተዋጊ ወታደርነት እስከ ጠቅላይ ኤታሞዦር ሹምነት ለ42 ዓመታት አገልግለዋል። ጄኔራል ሳሞራ የአራት ልጆች አባት ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም