ሕዝበ ሙስሊሙ የአብሮነት እሴት በማጠናከር ድርሻውን እንዲወጣ ምክር ቤቱ ጠየቀ

80

ጋምቤላ ግንቦት 27/ 2011 ሕዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር ያለውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር ለክልሉ ልማትና እድገት ድርሻውን እንዲወጣ የጋምቤላ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስገነዘበ፡፡

1440ኛው የኢድ አልፈ ጥር በዓል በጋምቤላ ስታዲዬም  ተከብሯል፡፡

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ዑመር ሽፋ እንዳሳሰቡት ሕዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር ያለውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር ለክልሉ ብሎም ለአገሪቱ ልማት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

በተለይም ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር የቆየውን የመቻቻልና የመከባበር እሴት በማጎልበት አገራዊ ለውጡን እውን ለማድረግ በጋ ራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዓሉን ሲያከብርም ህዝበ ሙስሊሙ የተራቡትን በመመገብ ፡የታረዙትን በማልበስ ፡የተቸገሩትን በመርዳትና በሌሎችም ለዘመናት የቆዩ እሴቶችን እንዲያጠናከር ጠይቀዋል፡፡

ከበዓሉ ታዳሚዎች አቶ አህመደልሀዲ አረቡ በሰጡት አስተያየት በዓሉ በተለይም ህዝበ ሙስሊሙ እንደ አገር አንድነቱን ያሳየበትና የክርስትና እምነት ተከታዮችም የመስገጃ ቦታዎችን በማጽዳት አብሮነታቸውን ያሳዩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር ወዳጅ ዘመዶችን ከመጠየቅ ባለፈ የተቸገሩትን በመርዳትየተራቡትን በመመገብና የታረዙትን በማልበስ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ሼህ መሀመድ መኪን ናቸው፡፡

በቀጣይም ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ያለውን የመቻቻልና የመከባበር እሴትን በማዳበር ለአገራችን ልማትና እድገት የምናደርገውን ጥረት እናጠናክራለን ብለዋል፡፡

ለበዓሉ ታዳሚዎች አካባቢውን ከማጽዳት ባለፈ ውሃና ሌሎች ነገሮችን ሲያድሉ ካገኘናቸው ወጣቶች መካከል ወጣት መስፍን ኤልያስ የከተማው ወጣቶች ተሳትፎውን ያደረጉት በሙስሊምና በክርስቲያኑ መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከር ታስቦ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በተለይም በሁለቱ እምነት ተከታዮች ጋር ያለውን የአብሮነት እሴት ለማጠናከር በቀጣይም መሰል ሥራዎችን እንደሚያጠናከሩ ገልጿል፡፡

የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ አቶ ኳት መንታፍ በበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳመለከቱት የእስልምና ኃይማኖት አባቶችና ተከታዮች የአካባቢውን ብሎም የአገሪቱን ሰላም አስጠብቆ ለማስቀጠል ድጋፋቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም