ችግኝ የመትከል ዕቅዱ በተለያየ ምክንያት በቢሊዮን የሚቆጠር ዛፍ ላጣችው ኢትዮጵያ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ችግኝ የመትከል ዕቅዱ በተለያየ ምክንያት በቢሊዮን የሚቆጠር ዛፍ ላጣችው ኢትዮጵያ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2011 በክረምቱ ወቅት ኢትዮጵያ የያዘችው ችግኝ የመትከል ዕቅድ ለአመታት በተለያየ ምክንያት የወደመውን የአገሪቱን ዛፍ ለመተካት ወሳኝ እንደሆነ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ገለጸ።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ፓውል ተርንቡል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተለያየ ምክንያት ለአመታት እየወደመ ያለውን የዛፍ ሃብት መተካት የሚያስችል መርሃ ግብር ነድፎ መስራት ያስፈልጋል።
ለማገዶ፣ ለከሰል፣ ለግንባታና ለእንስሳት መኖ ሲባል ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን የአገሪቱን የዛፍ ሃብት ከሰር ከስሩ መተካት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል ምክትል ዳይረክተሩ።
በመሆኑ በክረምቱ ጊዜ በመላ አገሪቷ በቢሊዮን የሚቆጠር የዛፍ ችግኝ ለመትከል የተያዘው ዕቅድና የተደረገው ዝግጅት ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል።
አገልግሎት ላይ የሚውለውን ዛፍ ለመተካት ዛፍ የመትከሉን ተግባር ማስቀጠል ካልተቻለ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ከመጋለጥም በላይ የተፈጥሮ ሃብት መመናመንን ሊያስከትል እንደሚችል አስገንዝበዋል።
የዛፍ መተከል የአፈር መሸርሸረን የሚከላከልና የውሃ ሃብትን ማሳደግ የሚችል በመሆኑም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ እየሰራው ባለው የልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር አማካኝነት ባከናወነው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ተግባርም ውጤት ማምጣቱን የገለጹት ፓውል ተርንቡል፤ በዚህም የማህበረሰቡን እሴት አሟጦ መጠቀም ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ድርጅቱ መሬትንና ውሃን በአግባቡ በመጠቀም በመሬትና ውሃ አስተዳደር ረገድ የላቀ ውጤት ማምጣት የቻለ እንደሆነም አስታውሰዋል።
በመላ አገሪቷ በቢሊዮን የሚቆጠር የዛፍ ችግኝ ለመትከት የሚያስችልና 40 ዛፍ በአንድ ሰው የሚል ብሔራዊ የአረንጓዴ ልማት የድርጊት መርሐ ግብር ተነድፎ ወደተግባር መገባቱ ይታወቃል።
የመርሃ ግብሩን ይፋ መሆን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለስራ ጉብኝት የመጡ የተለያዩ አገሮች መሪዎችና ሃላፊዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
በመርሐ ግብሩ 4 ቢሊዮን ችግኞችን በመጭው የክረምት ወቅት ለመትከል የታሰበ ሲሆን በዚህም 40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ ለመትከል ታቅዷል::