የህዝበ ሙስሊሙ አንድነት አገራዊና ህዝባዊ ሆኖ በዘላቂነት እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝበ ሙስሊሙ አንድነት አገራዊና ህዝባዊ ሆኖ በዘላቂነት እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
ግንቦት 27/2011 የህዝበ ሙስሊሙ አንድነት አገራዊና ሕዝባዊ ሆኖ በዘላቂነት እንዲቀጥል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጥሪ አቀረቡ።
1440ኛው የኢድ በዓል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የዑላማዎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
'ኢድ ማለት በየዓመቱ የሚመላለስ ደስታና ጸጋ ነው' ያሉት ተቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ፤ በዓመተ ሂጂራ ለ1440ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የኢድ በዓል ግን 'ደስታው እጥፍ ድርብ ነው' ብለዋል።
በዓሉ የሙስሊሙ ብሎም የአገር አንድነትና ሰላም የተረጋገጠበት፣ ባልተለመደ መልኩ በረመዳን ጾም በመንግስት ባለስልጣናት ኢፍጣር የተደረገበት፣ ክርስቲያኖች ለእስልምና እምነት ተከታዮች የመስገጃ ስፍራዎች ጽዳት ስራ ያከናወኑበት ልዩ በዓል መሆኑን አብስረዋል።
ይህ ትብብርና አንድነት ህዝባዊ፣ ኃይማኖታዊ፣ መንግስታዊ፣ አገራዊና ማህበረሰባዊ ሆኖ በዘላቂነት መቀጠል እንዳለበትም ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ጥሪ አቅርበዋል።
ለህዝበ ሙስሊሙና ህዝበ ክርስቲያኑ አንድነትና ሰላም መረጋገጥ ላበረከቱት ሚናም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምስጋና ችረዋል ተቀዳሚ ሙፍቲ።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በስፍራው ተገኝተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ በህዝበ ሙስሊሙ አንድነት የተከበረው የዘንድሮው ኢድ ልዩ ውበትና ድምቀት ያለው ነው ብለዋል።
'ጀነትን ለመውረስ ተዋደዱ፣ ተዛዘኑ' በሚለው የነብዩ መሃመድ አስተምህሮ መሰረት ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ጾምና ጸሎት ብቻ ሳይሆን አንዱ ላንዱ የሚያሳየው መልካምነትና መተዛዘን በከተማችን በተግባር ታይቷል ነው ያሉት።
ስለሆነም ህዝቡ በአንድነት፣ በሰላምና በመተባበር ለከተማዋ ውበትና ጽዳት መጠበቅ፣ በችግኝ ተከላና በሌሎች የበጎ ፈቃድ ስራዎች ትብብሩን የበለጠ እንዲያጠናክርና ተሳትፎውን እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል ኢንጅነር ታከለ።