ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ የክለቡን የቡድን መሪ ከስራ አሰናበተ

25
አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/8/2010 ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ የክለቡን የቡድን መሪ ማሩ ገብረፃዲቅ ከስራ ማሰናበቱን አስታወቀ። ትናንት በ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ጨዋታ የዳኛ ውሳኔ በመቃወም የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረፃዲቅ ዳኛውን መሬት ላይ በመጣል በቡጢ መማታቱ ይታወሳል። የክለቡ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለተከሰተው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ዋና ተጠያቂ የሆኑትን የቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረፃዲቅ ከስራቸው እንዲሰናበቱ ማድረጉን የክለቡ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳዊት አብርሃ ለኢዜአ ገልጸዋል። ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ ዳኛው ላይ ከበባ ያደረጉት የቡድኑ ተጫዋቾች ያደረጉት ተግባር "ፍጹም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ከበባውን ለፈጸሙ ተጫዋቾች ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን" ተናግረዋል። ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነት መሰል ተግባር የሚፈጽም ማንኛውም የክለቡ አባል ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ክለቡ የማይቆጠብ መሆኑን አስታውቀዋል። ክለቡ በተፈጠረው ስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለትና በተፈጠረው ክስተት ምክንያት ማዘኑን ነው አቶ ዳዊት ያስረዱት። እንዲህ አይነት መሰል ተግባራት በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ እንዳይፈጠሩ ለመከላካልም ክለቡ ጠንክሮ ይሰራል ብለዋል። የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ደጋፊዎች የተፈጠረውን የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት መቃወማቸው "ለስፖርታዊ ጨዋነት መስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ በመሆኑ" ክለቡ ለደጋፊዎች ምስጋና እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም