በደሴ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 45 ነጋዴዎች ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 45 ነጋዴዎች ተቀጡ
ግንቦት 27/2011 በደሴ ከተማ ያለ በቂ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 45 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የከተማው አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ሽመልስ ትላንት በሰጡት መግለጫ ከግንቦት ወር ጀምሮ የተከሰተው የኑሮ ውድነት የመልካም አስተዳደር ችግርን ፈጥሯል፡፡
የህብረተሰቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ መምሪያው ግብረ-ኃይል አቋቁሞ ባደረገው የገበያ ጥናትም የምርት እጥረት ሳይከሰት ነጋዴው ተመካክሮ ያለምክንያት የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ማረጋገጥ እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡
“የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ እንሰሳትና የእንሰሳት ተዋዕጾ ምርቶች ላይና ምግብ ቤቶች ላይ ከወጭ ቀሪ 15 በመቶ ማትረፍ ሲገባቸዉ ከ100 ፐርሰንት በላይ በማትረፍ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት በማድረግ ህብረተሰቡ እንዲማረር አድርገዋል”ብለዋል፡፡
“ይህን ባደረጉ 45 ነጋዴዎች ላይ የጹህፍ ማስጠንቀቂያ ከመሰጠቱም በላይ በማሸግና በህግ እንዲጠየቁም ተደርጓል”ብለዋል፡፡
እርምጃ የተወሰደው በምግብ ቤቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ ቸርቻሪዎች፣ በተለያዩ እህሎችና ስጋ ነጋዴዎች ላይ መሆኑን አስታውው ግብረ ኃልሉ ገበያውን ለማረጋጋት ከተለያዩ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የሚመጡ ምርቶች ላይ ጥናት በማድረግ የዋጋ ማሻሻያ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡
በንግድ ቤቶች ላይ የተሸሻለውን የዋጋ ዝርዝር በመለጠፍም ህብረተሰቡ የሚገዛውን ማንኛውንም ምርት ህጋዊ ማህተም ያለውን በማየት መብቱንም ማስከበር ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የዋጋ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ምርቶች መካከል ጤፍ ከ3ሺህ ብር በላይ የነበረውን በደረጃ ከሁለት ሺህ 100 እስከ ሁለት ሺህ 500 ብር፣ ስጋ እስከ 350 የነበረው በደረጃ ከ220 እስከ 280 ብር ዝቅ ብሎ እንዲሸጥ መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡
አትክልትና ፍራፍሬም ከ19 እስከ 25 ብር የነበረውን ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቡካዶና ሌሎችንም እስከ 50 ብር ድረስ ይሸጡ ስለነበረ ወደ በፊቱ ዋጋ ዝቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በግንቦት ወር ላይ ብቻ ይህን ያህል ዋጋ የሚያስጨምር ምክንያት አለመኖሩም በጥናት ተረጋግጦ ወደ ነበረበት እንዲመለስ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የጹህፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸዉ ነጋዴዎችም እስከ ሰኔ 5/2011 ዓ.ም ድረስ ካላስተካከሉ ንግድ ፍቃድ መቀማትና የማሸግ እርምጃ ይከተላቸዋልም ብለዋል፡፡
“አንሶላ ሳይቀይሩ፣ ቀለም ሳይቀቡና ለቤቱ ማሻሻያ ሳያደርጉ የዋጋ ጭማሬ ባደረጉ አልጋ ቤቶች ላይም እርምጃ ለመውሰድ በጭማሪ የተጠረጠሩ 70 አልጋ ቤቶች ተለይተዋል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በኋላም ያለአግባብ በአቋራጭ ለመክብረ የሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎችን አጋልጦ በመስጠት የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡