ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዓመት በፊት የሰው ልጅ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ ቁሳቁሶች ተገኙ

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዓመት በፊት የሰው ልጅ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ ቁሳቁሶች መገኘታቸው በተመራማሪዎች ይፈ ተደረገ።

ቁሳቁሶቹ የተገኙት በአፋር ክልል ልዩ ስሙ በኮል ዶራ በተባለ ቦታ ከኢትዮጵያና ከአሜሪካ የተውጣጡ የጥናት ቡድኖች ባደረጉት የአምስት ዓመት የዳሰሳ የቁፋሮ ጥናት ነው። 

የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር ዴቪድ ብራውን እንዳሉት ግኝቱ ከአሁን በፊት የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የድንጋይ ቁሳቁሶችን ተጠቅሟል ተብሎ ከተያዘው አመት ከ50 እስከ 100 ሺህ ዓመት ሊቀድም ይችላል። 

እስካሁን በዓለም በተደረገው ተመሳሳይ ጥናት በኬንያ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዓመት የሆነው የድንጋይ ቁሳቁስ የተገኘ ቢሆንም ቁሳቁሶቹን የተጠቀሙበት ግን እንሰሳት ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ጥናቶች ያሳያሉ። 

ይሁን እንጂ በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው ከዛሬ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዓመት በፊት የሰው ልጅ ድንጋይን ጠርቦ ለተለያዩ ተግባራት እንደተጠቀመበት የሚያሳይ ነው ። 

ይህም የሰው ልጅ ድንጋይን ጠርቦ ለተለያዩ አገልግሎቶች  መጠቀም የጀመረው ከ2 ነጥብ 55 እና 2 ነጥብ 58 ሚሊዮን ዓመት በፊት ነው የሚለውን ጥናት ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ዓመት ወደ ፊት የሚያስኬድ ነው። 

የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ሙሉጌታ ፍሰሃ በበኩላቸው ግኝቱ ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለዓለም የምርምር ዘርፍ ትልቅ ሚና ያለው ነው። 

ከሳይንሳዊ ጥናት ጠቀሜታው ባለፈም እነዚህ ቦታዎች የዓለም የምርምር ትኩረትና የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው ዓለም አቀፍ አካላት መዳረሻ መስህብ እንዲሆኑ በማድረግ ለአካባቢውና ለአገር የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆንም እንሰራለን ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም